የአፍሪካ የኢኮኖሚ ነፃነት ትልም – ከጥሬ ዕቃ ጥገኝነት ወደ አሕጉራዊ አቅም

6

 

አፍሪካ የዓለምን የተፈጥሮ ሀብት ክምችት ከፍተኛውን ድርሻ ይዛለች። ጥሬ ዕቃዎች እሴት ሳይጨመርባቸው ወደ ውጭ የመላክ የቅኝ ገዢነት አስተሳሰብን የተከተለ የንግድ ሥርዓት ሰለባ መኾኗ ግን ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነቷን አደጋ ላይ ጥሎታል።

የተባበሩት መንግሥታት የንግድ እና ልማት ድርጅት መረጃዎች እንደሚያሳዩት አፍሪካ ከወጪ ንግድ ከምታገኘው ገቢ ውስጥ አብዛኛውን ድርሻ የሚይዘው ያልተቀነባበሩ ማዕድናት እና የግብርና ምርቶች ንግድ ነው። ይህ አሠራር አፍሪካን የዓለም አቀፍ የዋጋ ግሽበት፣ የገበያ መዋዠቅ እና የውጭ ኀይሎች የጂኦፖለቲካ ጫና ሰለባ አድርጓታል።

ኬንያዊው ጠበቃ እና ምሁር ፕሮፌሰር ፓትሪክ ሉሙምባ እንደሚሉት አፍሪካ ከጥሬ ዕቃ ላኪነት ወጥታ ወደ ሀገር ውስጥ የእሴት ማሻሻያ እና የኢንዱስትሪ ልማት በመሸጋገር ባላት ጸጋ ልክ ተጠቃሚ መኾን ይኖርባታል።

በማቀነባበር፣ በፈጠራ እና በጥራት ላይ ኢንቨስት ማድረግ ሥራዎችን መፍጠር፣ ኢንዱስትሪዎችን መገንባት እና የአህጉሪቱን ኢኮኖሚም መቀየር ይገባል።

ብሉምበርግ እንደዘገበው ዴሞክራቲክ ሪፐብሊክ ኮንጎ ለዓለም ኤሌክትሪክ ተሽከርካሪዎች እና ቴክኖሎጂዎች አስፈላጊ የኾነውን ኮባልት እና መዳብ ታመርታለች፤ ነገር ግን ማዕድኑ ያለ እሴት ማሻሻያ ስለሚወጣ ከሀብቱ የሚገኘው ትርፍ እጅግ አነስተኛ ነው።

የኢትዮጵያ የወርቅ እና የግብርና ምርቶች (ለምሳሌ የቡና) ሀብት ያለ በቂ የሀገር ውስጥ ማቀነባበሪያ ኢንዱስትሪዎች ሲመረት ቆይቷል።

የእሴት ማሻሻያ ፖሊሲዎችን ተግባራዊ ማድረግ የኢኮኖሚ ነፃነትን ብቻ ሳይኾን ከሰላም እና ጸጥታ መዋቅር ጋር በቀጥታ የተያያዘ ነው።

እንደ ስቶክሆልም ዓለም አቀፍ የሰላም ጥናት ተቋም መረጃ በአፍሪካ የሚገኙ በርካታ ግጭቶች እና የእርስ በርስ ጦርነቶች ከሀብት ምንጮች ቁጥጥር፣ ከሕገወጥ የማዕድናት ንግድ እና ከአካባቢያዊ ብዝበዛ ጋር የተሳሰሩ ናቸው።

ማዕድናት ያለአግባብ በውጭ ኩባንያዎች ሲዘረፉ እና የአካባቢው ማኅበረሰብ ተጠቃሚ ሳይኾን ሲቀር የሚፈጠረው ኢኮኖሚያዊ አለመረጋጋት ለአመጽ እና ለሽብር ቡድኖች መሠረት ይኾናል።

የአፍሪካ ኅብረት ያወጣው “የአፍሪካ ማዕድን ራዕይ” አህጉሪቱ ያላትን የተፈጥሮ ሀብት ለዘላቂ ልማት እና ለሰላም ግንባታ ማዋል የሚያስችል ስልታዊ ማዕቀፍ ያስቀምጣል።

ርዕዩ ጥሬ ዕቃዎችን በሀገር ውስጥ በማቀነባበር የሥራ ዕድል መፍጠር፣ የቴክኖሎጂ ሽግግር ማድረግ እና የሀገር ውስጥ ገበያን ማጠናከር እንደሚገባም ይደነግጋል።

አፍሪካ ከታሪካዊ የርካሽ ጥሬ ዕቃዎች ላኪነት ወደ አምራች እና የዕውቀት ላይ የተመሠረቱ አገልግሎቶች አቅራቢነት እንድትሸጋገር የማዕድን ሴክተሩን ገለልተኛ እና የተዘጋ ሁኔታ መክፈት ያስፈልጋል።

የዘንድሮው የጣና ፎረም ዋነኛ መሪ መልዕክት እንደሚያሳየው ኢኮኖሚያዊ ሉዓላዊነት ሳይረጋገጥ ዘላቂ ሰላም ማምጣት አይቻልም። በመኾኑም አፍሪካውያን መሪዎች እና ፖሊሲ አውጪዎች የውጭ ገበያ ጥገኝነትን የሚሰብሩ፣ የክልል ነፃ የንግድ ቀጣናዎችን የሚያጠናክሩ እና የሀገር ውስጥ የኢንዱስትሪ መሰረቶችን የሚገነቡ ጽኑ ፖሊሲዎችን መተግበር ይጠበቅባቸዋል።

#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#Ameco #RawToRefined #AfricaSovereignty
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_13_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleየምሥራቅ ዕዝ ሬጅመንት በፋርጣ ወረዳ ለሚገኙ አርሶ አደሮች ሰብል ሠበሠበ።
Next articleጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የመገጭ መስኖ ግድብን መረቁ።