
ኢትዮጵያውያን ከጥንት አባቶች ጀምሮ ሀገርን በደም እና በአጥንት አጽንተው ለትውልድ የማስረከብ ታሪካዊ አደራን ይዘው የመጡ ሕዝቦች ናቸው። በየዘመናቱ የሀገርን ሉዓላዊነት እና የሕዝቦችን ሰላም ለማስጠበቅ በሚከፈለው መራራ ዋጋ ውስጥ የሀገር መከላከያ ሠራዊት በየአውደ ውጊያው የሚፈጽመው ተጋድሎ የዚሁ ታላቅ ታሪክ ህያው ማሳያ ነው።
ታዲያ የኢትዮጵያ ሕዝብ ለሠራዊቱ ያለው አክብሮት በደም ስሩ ውስጥ የተዋሃደ ትውልዳዊ እሴት ነው። ሠራዊቱ ሀገር ለማጽናት እና የዜጎችን እፎይታ ለማረጋገጥ በየጊዜው የሚከፍለውን ከፍተኛ መስዋዕትነት በመገንዘብ ሕዝቡ በየወቅቱ በአደባባይ ወጥቶ የሚያደርገው ሰላማዊ ሰልፍ እና ሁለንተናዊ የሞራል ድጋፍ የዚህ የማይበገር ሀገራዊ አንድነት ማረጋገጫ ነው።
እርሱ በማንኛውም አስቸጋሪ የአየር ጸባይ እና አስቸጋሪ መልከዓምድር ውስጥ ኾኖ የሀገርን ጥሪ የሚመልስ፣ የተደቀኑትን ፈተናዎች ወደ አስተማማኝ ድል የሚቀይር ትልቅ ሀገራዊ ኩራትም ነው።
እርሱ የሀገሪቱን ድንበር እና የአየር ክልል እንዳይደፈር ከመጠበቅ ባሻገር የዜጎች የዕለት ተዕለት ሕይወት በሰላም እንዲቃኝ የሚያደርግ ጋሻ ነው።
የሠራዊቱን ዝግጁነት እና ተቋማዊ ጥንካሬውን ማጎልበት ለሀገሪቱ ዘላቂ ዕድገት ብቻ ሳይኾን ሙሉው የቀጣናው ሰላም እንዲጠበቅ አስተማማኝ መሠረት ነው።
የጦር ኀይሎች ጠቅላይ ኤታማዦር ሹም ፊልድ ማርሻል ብርሃኑ ጁላ እንደገለጹት “ይህንን መስዋዕትነት ከፋይ እና ታላቅ ተቋም ማክበር እና ድጋፍ መስጠት ኢትዮጵያን የማክበር እና የመውደድ ህያው መግለጫ ነው!”
በመኾኑም ሁሉም ከጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ጎን በጽናት በመቆም አጋርነትን ማሳየት የሀገርን ህልውና እና የወደፊት ተስፋ ማጽናት መኾኑን በመገንዘብ ድጋፍን አጠናክሮ ማስቀጠል እንደሚገባም ነው ያስረዱት።
ሠራዊቱን ማክበር ሀገርን የማክበር ህያው መግለጫ ነውና ሕዝቡም ለጀግናው የመከላከያ ሠራዊት ያለውን የማያወላውል ክብር እና ድጋፍ በአደባባይ ወጥቶ እያንጸባረቀ ይገኛል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
