በ12ኛው የጣና ፎረም ምክንያት በባሕር ዳር ከተማ ለትራፊክ ዝግ የሚኾኑ እና አማራጭ መንገዶች ይፋ ተደረጉ።

15
ጥቅምት 13/2019 ዓ.ም እና ጥቅምት 15/2019 ዓ.ም በባሕር ዳር ከተማ በሚካሄደው 12ኛው የጣና ፎረም ዓለም አቀፍ ጉባኤ ላይ የሚታደሙ የክብር እንግዶችን አቀባበል እና ሽኝት ለማቀላጠፍ፣ ከኤርፖርት እስከ ጊዮርጊስ ቤተ ክርስቲያን አደባባይ ያለው ዋና መንገድ ለተሽከርካሪዎች ዝግ መኾኑን የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ፖሊስ መምሪያ አዛዥ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው ገልጸዋል።
ኮማንደር ዋለልኝ የከተማዋ ነዋሪዎች እና አሽከርካሪዎች የዕለት ተዕለት እንቅስቃሴአቸው እንዳይስተጓጎል እንዲሁም የትራፊክ ፍሰቱ ሰላማዊ ኾኖ እንዲቀጥል የሚከተሉትን አማራጭ መንገዶች እንዲጠቀሙ ጥሪ አቅርበዋል።
ከአባይ ማዶ ለሚመጡ አሽከርካሪዎች፦ በአሮጌው ድልድይ አድርገው በሚመጡበት ወቅት የአልማ ወተር ፍሮንት መስመርን መጠቀም ይችላሉ።
ከመሀል ከተማ ወደ ገጠር መንገድ ለሚንቀሳቀሱ፦ በአዝዋ አድርገው ወደ ሙሉ ዓለም፣ በሰርፀ ጀርባ ቀጥታ ወደ 6ኛ ዋና ፖሊስ ጣቢያ በሚያስወጣው ዋና የኮብልስቶን መንገድ በማለፍ፣ የድሮውን አልካን አቋርጠው ወደ ኃይሌ ትምህርት ቤት እና ቀጥታ ወደ ዮሐንስ ቤተ ክርስቲያን መጓዝ ይችላሉ።
ከገጠር መንገድ ተነስተው ወደ ከተማ ለሚገቡ፦ በጎፋ ካቶሊክ ሆስፒታል በኩል አድርገው ዲፖን በመቁረጥ የኪዳነ ምህረት መስመርን መጠቀም ይችላሉ።
በኤርፖርት መስመር ለሚንቀሳቀሱ፦ ዋናውን የተባበሩት እና ጽራፂዮን ማርያም መስመርን በመጠቀም፣ በኢላ ማደያ በኩል አልፎ በማርዳ እብነ-በረድ 40 ሜትር አስፓልት ወደ ዋናው መስመር መግባት ይቻላል።
በተጨማሪም የኤርፖርት ታክሲዎች ጊዜያዊ ማቆሚያ (ፌርማታ) በአልማ ወተር ፍሮንት መንገድ ላይ ለፓርኪንግ በተዘጋጀው ቦታ እንዲኾን መደረጉን የፖሊስ መምሪያ አዛዡ ጠቁመዋል።
በሌላ በኩል ጉባኤው ተጀምሮ እስኪጠናቀቅ ባሉት ቀናት በጣና ሐይቅ ላይ ምንም አይነት የጀልባ እንቅስቃሴ የማይኖር በመኾኑ፣ የወደብ አካባቢ ማኅበረሰብ፣ የጀልባ አሽከርካሪዎች እና ተገልጋዮች አስፈላጊውን ቅድመ ዝግጅት እንዲያደርጉ ኮማንደር ዋለልኝ ቢምረው አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየኢትዮጵያ የማይበገር ጽናት እና የባሕር በር የባለቤትነት አጀንዳ።
Next articleየሠራዊቱ ታሪካዊ ውለታ እና የሕዝብ አለኝታነት!”