ኢትዮጵያውያን መብታቸውን እና ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ ሲነሱ የሚፈጥሩት የኀይል ማዕበል ፍጹም የማይበገር እና ታሪክ የሚመሰክረው ሐቅ ነው።

የሕዝቡ አንድነት እና የባሕር በር ጥያቄ:- ከሰሞኑ በተካሄዱት ሕዝባዊ ሰልፎች የተስተጋቡት “ቀይ ባሕር፣ አሰብ እና ከግድቡ ወደ ወደቡ የሚሉ ሐሳቦች የኢትዮጵያውያንን የህልውና ጥያቄ እና የባሕር በር ፍላጎት በግልጽ ያሳያሉ። እነዚህ መልዕክቶች ተራ የእርስት ጥያቄ ብቻ ሳይኾኑ የታሪክ፣ የኢኮኖሚ እና የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍትሕ ጥያቄዎች ናቸው።
የታሪክ ምሁሩ ፕሮፌሰር አየለ በከሪ የሚያረጋግጡትም ኢትዮጵያውያን ከባሕር ተለይተው እንደማያውቁ እና ባሕር የሕልውናቸው አካል መኾኑን ነው።

የማይበገር ጽናት እና ታሪካዊ ሐቅ:- ኢትዮጵያውያን ሲነካኳቸው ቁጣቸው የሚጨምር፣ ሲገፏቸው ደግሞ ልዩነታቸውን በመጥረግ አንድነታቸው ከማንኛውም ጊዜ በላይ በጽኑ ዓለት ላይ የሚመሠረት ሕዝብ መኾናቸውን በድጋሚ አረጋግጠዋል። በታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ ላይ ያሳዩት ተምሳሌታዊ አንድነት ሕዝቡ ለጋራ ዓላማ ሲቆም ማንም ሊበግረው የማይችል አቅም እንዳለውም በዓለም ፊት አሳይቷል።

ለተቀናቃኞች የተሰጠ ግልጽ መልዕክት:- ውስጣዊ ችግሮች አሉባቸው ብለው ለሚያስቡ እና የኢትዮጵያን ድክመት ጥግ ይዘው ለሚጠብቁ ኀይሎች በሰልፎቹ የተሰነዘረው መልዕክት ግልጽ ነው። ፕሮፌሰር አየለ እንደሚሉት ግብጽ ኢትዮጵያ ወደ ውኃው እንዳትደርስ ከፍተኛ ዘመቻ እያካሄደች እንደምትገኝ ተናግረዋል። ሕዝቡ በታላቁ ግድብ ያሳየውን ተአምራዊ ድል ዛሬም በሌሎች የሉዓላዊነት እና የልማት ምዕራፎች ላይ ለመድገም ፍጹም ዝግጁ መኾኑን አሳይቷል።

የብልጽግና እና የወደብ ጉዞ:- የኢትዮጵያ ጠላቶች የውስጥ ውጥንቅጦችን እንደ ማዳከሚያ መሳሪያ ሊጠቀሙ ሲሞክሩ ሕዝቡ ግን ከብረት የጠነከረ አንድነቱን በማሰለፍ የውጭ ግፊቶችን ድል አድርጎ እንደሚያልፋቸው አስመስክሯል። ከግድቡ ወደ ወደቡ የሚደረገው ጉዞ የኢትዮጵያ የብልጽግና እና የባሕር በር ባለቤትነት እውን መኾን የማይቀር ታሪካዊ እውነት መኾኑን የሚያበስር ነው።
ፕሮፌሰር አየለ የኢትዮጵያ ታሪክ በ1991 እና በ1993 ዓ.ም እንዳልተጀመረ እና ወጣቱ ታሪኩን አውቆ አጀንዳው ዘላቂ ምላሽ እስኪያገኝ ድረስ በቁርጠኝነት ሊሠራ ይገባል ብለዋል።

ዘጋቢ:- ስማቸው አጥናፍ