
የጣና ዳሯ እመቤት በኢትዮጵያዊነት ባሕል ደግሳለች፤ በኢትዮጵያዊነት ባሕል ደምቃለች፣ በኢትዮጵያዊነት እሴት አብባለች፣ ከውበት ላይ ውበት ደራርባለች፣ ቄጠማውን ጎዝጉዛለች፡፡ በኢትዮጵያዊነት አሸብርቃለች፡፡
ጥቁሮች በጋራ፣ ስለ ጋራ ይመክራሉ፣ የምድራቸውን እሾህ፣ በምድራቸው ጥበብ ይነቅላሉ፣ የምድራቸውን ጥበብ በምድራቸው ያፈስሳሉ፣ የምድራቸውን አቅም በምድራቸው ይጠቀማሉ፣ ስለ ችግሮቻቸው መክረው፣ መፍትሔዎቻቸውን ያስቀምጣሉ፣ መውጫ መንገዱን ይቀይሳሉ፣ መሻገሪያ ድልድዩን ያበጃሉ፡፡
ጥቁሮች ባለ ጸጋ ሳሉ እንደ ደሃ ተቆጥረዋል፣ ጀግኖች ሳሉ እንደ አቅመ ቢስ ታይተዋል፣ ነጻ ኾነው ሳለ ነጻነታቸውን እንዲያጡ ተደርገው ኖረዋል፣ ጠቢባን ሳሉ የማያውቁ ተብለዋል፣ ቀዳሚዎች ኾነው ኋላ ቀር ተደርገዋል፣ ባለ ታሪክ ኾነው ሳለ ታሪክ የለሽ ተብለዋል፡፡
በምድራቸው ተሳድደዋል፣ በቀያቸው ተገፍተዋል፣ በማንነታቸው፣ በቆዳ ቀለማቸው ብቻ የስቃይን ጥግ አይተዋል፣ ሃብት እና ንብረታቸውን ተወርሰው፣ ለወራሾቻቸው አገልጋዮች ኾነው ኖረዋል፡፡ እንደ ሸቀጥ ተሽጠዋል፣ በገንዘብ ተለውጠዋል፣ ከሚወዷት ቀያቸው ርቀው በባዕዳን ሀገር አንገት ደፍተው ኖረዋል፡፡
ከጥቁሮች መካከል የጠነከሩት፣ አሻፈረኝ ያሉት፣ ለጠላት ያልተበገሩት፣ በትዕቢት የመጣውን ጠላት አሳፍረው የመለሱት ግን ክብራቸውን አላስነኳትም፣ ቀያቸውን አላስደፈሯትም፡፡ የራሳቸውን ቀዬ አስከብረው፣ የተነሳባቸውን ጠላት ሰባብረው በግፍ ለነበሩት ደርሰውላቸዋል፣ በባርነት የታሰሩትን ምሳሌ እና ምልክት ኾነዋቸዋል፡፡
ነጮች በአፍሪካውያን ላይ የግፍ ግፍ ሲያደርሱ ኢትዮጵያ ከሌሎች ተነጥላ የነጮችን ክንድ የሰበረች፣ ክብሯን በክንዷ ያስከበረች፣ የነጭን ያልተገራ ግስጋሴ የገታች፣ በአሻገር ያለውን የቀኝ ገዢ ስብስብ ያስደነገጠች፣ አካሄዱን ያስቀየረች ኩሩ ሕዝቦች፣ ጀግና ልጆች ያሉባት ሀገር ናት፡፡
ኢትዮጵያ ነጭን አሸንፋ ጥቁሮች አሸናፊዎች እንደኾኑ አሳየች፣ በልጆቿ መትታ በጥቁሮች ምድር ማንም አይደፍረኝም ያለውን ነጭ አስደነገጠች፣ አንገቱን አስደፋች፣ ኢትዮጵያ በድቅድቅ ጨለማ ለነበሩት የከፍታ መብራት ኾነች፣ መንገድ ለጠፋባቸው መሪና አሻጋሪ ተባለች፡፡
አትንኩን አንነካችሁም በሚለው መርኋ በግፍ የሚነኳትን ትሰባብራለች፣ በፍቅር የሚቀርቧትን በፍቅር ታቅፋለች፣ ከፍ ከፍ አድርጋ ታከብራለች፣ ኢትዮጵያ በዓለም ላይ ላሉ ጥቁሮች ምልክታቸው፣ መመኪያቸው፣ የድል መንሻቸው፣ ሲደክሙ ምርኩዛቸው፣ ሲያዝኑ መረጋጊያቸው፣ የተስፋ መንገድ ባጡ ጊዜ ተስፋቸው ናት፡፡ ተከብራ አስከብራቸዋለች፣ ቀድማ አስቀድማቸዋለችና፡፡
እነሆ በነጭ እጅ ውስጥ የነበሩት ጥቁሮች ሰንሰለቱን በጣጥሰዋል፣ ትብታቡን ፈትተዋል፣ በምድራቸው፣ በጥበባቸው የራሳቸውን ታሪክ እየጻፉ ነው፡፡ ዛሬ ከዳር ዳር እየተጠራሩ ለችግሮቻቸው የራሳቸውን መፍትሔ እያስቀመጡ ነው፡፡ ከታላቁ ኅብረታቸው ከአፍሪካ ኅብረት ጀምሮ በሌሎች መገናኛ መድረኮች ስለ ራሳቸው ይመክራሉ፣ ይዘክራሉ፡፡ ለመሰባሰቢያ፣ ለመመካከሪያ፣ ለመፍትሔ ማዘጋጃ የምትመረጠው ደግሞ በነጻነት፣ በኩራት፣ በአንድነት የኖረችው ኢትዮጵያ ናት፡፡
ጥቁሮች ችግሮቻቸውን የሚፈቱበት፣ ተስፋዎቻቸውን የሚያስቀጥሉበት፣ አንድነታቸውን የሚያጠናክሩበት ምክክር በዚህችው በኢትዮጵያ ምድር፣ በጣና ዳሯ እመቤት በባሕር ዳር ያደርጋሉ፡፡ ጣና ከቸረው ዓሳ እየቀመሱ፣ በጣና ዳር መንፈሳቸውን እያደሱ፣ በጣና ላይ እየተመላለሱ በአንድነት ይዋባሉ፡፡ ስለ ጋራ ደኅንነታቸው ይመክራሉ፣ ክብራቸውን ስለሚያስጠብቁበት ጉዳይ ይወያያሉ፡፡
የጣና ዳሯ እመቤት፣ የግዮን ንግሥት፣ ልምላሜ በማይለያቸው ዘንባባዎቿ፣ በጠሩት ጎዳናዎቿ፣ ጎብኞቿን ታስደስታለች፡፡ በአሻገር የሚያይዋትን ታማልላለች፣ በፍቅሯ አሥራ ታስቀራለች፣ በትዝታዋ ታንከራትታለች፡፡
ቢሻው ከቤዛዊት ከቤተ መንግሥቱ፣ ቢሻ ከጣና ከገዳማቱ እና ከአድባራቱ፣ ቢፈልግ ከጭስ ዓባይ ከፏፏቴው፣ እንዲያም ቢል ድባንቄ ከከፍታው እየሄዱ ታሪክ የሚማሩባት፣ ጥበብ የሚያዩባት፣ ውበት የሚያደንቁባት፣ መንፈስን የሚያድሱባት ውብ ከተማ ናት፡፡
ተዝናኖት የፈለጉት በታንኳ በጣና ይመላለሳሉ፣ ድንቅ ተፈጥሮን ማየት ያማራቸው ዓባይ በጣና ላይ የሚያልፍበትን እያዩ ይደነቃሉ፣ ሌላ ዓለም ላይ በማያገኙት ድንቅ ውበት ይደመማሉ፣ ታሪክ እና ሃይማኖት መማር የፈለጉት ወደ ገዳማቱ እና አድባራቱ እየተጓዙ የረቀቀ ሃይማኖት ያያሉ፣ ከጠለቀው ታሪክ ይቀስማሉ፡፡ ወደ ጭስ ዓባይ የሚጓዙት ውኃ ድንቅ ውበት ሢሠራ ይመለከታሉ፡፡
ባሕር ዳር ታይተው የማይጠገቡ ድንቅ ውበቶች አሏት፡፡ በቀን የሚዝናኑባቸው፣ በምሽት የሚያርፉባቸው ዘመኑን የዋጁ ሆቴሎች፣ ሐሴት የሚያደርጉባቸው ሥፍራዎች ሞልተዋታል፡፡ አፍሪካውያን አምሳለ ልብ በኾነው በጣና ሐይቅ ያለውን ካዩ ጥቁሮች ከሁሉም የቀደሙ፣ የከበሩ፣
በታሪክ ያበቡ፣ ለዓለም በጥበብ የሚያበሩ እንደሆኑ ይረዳሉ፡፡ በገዳማቱ ውስጥ ትናንትን፣ ዛሬን እና ነገን የሚያሳዩ፣ ምስጢር የበዛባቸው፣ ጥበብ የመላባቸው የከበሩ ቅርሶች አሉና፡፡ በዚያ ውስጥ ኢትዮጵያ ቀደምት እንደሆነች፣ በታሪክ እንደከበረች፣ በምስጢር እንደተከበበች፣ በጥበብ እንዳጌጠች፣ ለምስክርነት እንደተቀመጠች፣ ተስፋ እንደሆነች ያያሉ፡፡ የጥቁርን ታሪክ አይተው ጥቁሮች ይደሰታሉ፡፡
እመቤቷ፣ ውቢቷ ባሕር ዳር ሊመክሩባት፣ ሊሰነብቱባት፣ አንድነታቸውን ሊያጸኑባት የሚመጡትን እንደ ቀደመው ሁሉ አቅፋ እየተቀበለች፣ እንኳን መጣችሁልን እያለች ታሞናሙናቸዋለች፡፡ በደስታ ከፍ ከፍ ታደርጋቸዋለች፡፡ የባሕር ዳር ጎዳናዎች ደምቀዋል፣ አሸብርቀዋል፣ ከዓመት እስከ ዓመት እንግዳ መቀበል ልማዳቸውና ባሕላቸው የሆኑት የባሕር ዳር ነዋሪዎች የእንግዳ ማረፊያዎቻቸውን አሳምረዋል፡፡
አፍሪካውያን ዓይኖቻቸውን ባሕር ዳር ኢትዮጵያ ላይ ያደርጋሉ፣ ታላቁን ጣናን ይመለከታሉ፣ ኃያሉ ግዮን (ዓባይን) ያያሉ፣ ከጣና ዳር በጣና ውይይት (ፎረም) የሚመከረውን ይሰማሉ፡፡
ጥቁሮች ራሳቸው፣ ስለ ራሳቸው ይመክራሉ፣ መፍትሔዎቻቸውን ያስቀምጣሉ፣ ተስፋዎቻቸው እውን እንዲሆኑ ይጥራሉ፣ ስለ ኢትዮጵያ ያዩትን፣ የተመለከቱትን፣ በየደረሱበት ይናገራሉ፡፡
የጣና ዳሯ እመቤት እንግዶቿን ለቀናት በውብ መስተንግዶ ታስተናግዳለች፣ እንዳይረሱት አድርጋ ትዝታ ትጥልባቸዋለች፣ በአሻገር ኾነው ስለኢትዮጵያ መልካም የማያወሩትን መልካም አድርጋ ታሳያቸዋለች፡፡
የጥቁሮች ውይይት በጣና ዳሯ እመቤት ነገ ይጀመራል፣ ከፍ ባለችው ሀገር ኢትዮጵያ ከፍ ያለ ምክር ይመከራል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
