
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክትን በይፋ መርቀው ሥራ አስጀምረዋል። ይህንን አስመልክተው ያስተላለፉት መልእክት ሙሉ ይዘት እንደሚከተለው ቀርቧል፦
በዛሬው ዕለት ለታሪካዊቷ ጎንደር እና ለአካባቢዋ ማህበረሰብ ትልቅ የምስራች የሆነውን የመገጭ መስኖ ግድብ ፕሮጀክት በይፋ መርቀን ለአገልግሎት አብቅተናል። ይህ ፕሮጀክት ረጅም ዓመታት የዕቅድና አተገባበር መጓተት ቢፈታተነውም፣ በመደመር እሳቤ የአፈጻጸም ችግሮቹን በመፍታት ወደ ታላቅ በረከት መለወጥ ችለናል።
ይህ ግድብ 185 ሚሊዮን ሜትር ኩብ ውሃ የመያዝ አቅም ያለውና ከ17 ሺህ ሄክታር በላይ መሬትን በመስኖ በማልማት በአካባቢው የሚኖሩ በአስር ሺዎች የሚቆጠሩ አርሶ አደሮችን በቀጥታ ተጠቃሚ በማድረግ የአካባቢውን ነዋሪዎች የልማት ጥያቄ በዘላቂነት መመለስ የሚያስችል ታላቅ ፕሮጀክት ነው። ግድቡ ለጎንደር ከተማና በዙሪያዋ ላሉ ከተሞች አስተማማኝ ንፁህ የመጠጥ ውሃ ከማቅረብ ባለፈ፣ ሁለንተናዊ የኢኮኖሚ መነቃቃትን ይዞ የመጣ ነው። በግድቡ ሰው-ሰራሽ ሀይቅ ዙሪያ የሚስፋፉት የከተማ ግብርና፣ መጠነ-ሰፊ የአሳ እርባታ፣ እንዲሁም ለቱሪዝም ልማት የሚሆኑ የመዝናኛ ሪዞርቶች እና ሎጆች ለአካባቢው ወጣቶች ሰፊ የስራ ዕድል የሚፈጥሩና የንግድ እንቅስቃሴውን የሚያሳድጉ ናቸው።
ይህን ስኬት ለእይታ ለማብቃት በጥብቅ ክትትልና ድጋፍ እውን ማድረግ የቻልን ቢሆንም፣ ጎንደር ገና ብዙ ሊሰራላት የሚገባ ከተማ እንደመሆኗ ህዝቡ በልማቱ ላይ በንቃት እንዲሳተፍ ጥሪዬን አቀርባለሁ። የኢትዮጵያ እድገት ሁሉንም አካባቢዎች ያካተተና ሁሉንም ዜጋ እኩል የሚያቅፍ እንዲሆን በትጋት መስራታችንን እንቀጥላለን!
