
ባለፉት የለውጥ ዓመታት ኢትዮጵያ የወሰደቻቸው ሪፎርሞች የሀገሪቱን ፖለቲካዊ፣ ኢኮኖሚያዊ እና ማኅበራዊ መሠረቶች በአዲስ መልክ ያነጹ ታሪካዊ እርምጃዎች ናቸው።
“በትላንት ታሪክ ላይ ቆመን የዛሬን ፈተና በመሻገር ብሩህ ነገን እንገነባለን” የሚለው የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ርዕይም ለዚህ ሀገራዊ ትንሳኤ ጽኑ መሠረት ኾኗል። ባለፉት ዓመታትም የኢትዮጵያን ሁለንተናዊ ከፍታ የሚያረጋግጡ ተግባራዊ ስኬቶች መመዝገባቸውን ተናግረዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት አግላይ የኾነውን የዳር እና መሐል ፖለቲካዊ ክፍፍል በመስበር የዜጎችን እኩል የባለቤትነት ስሜት የሚያረጋግጥ ጠንካራ ኅብረ ብሔራዊ አንድነት ተገንብቷል።
ታሪክን ከማውገዝ ወይም ከማምለክ ጽንፍ በመውጣት ጥላቻን በይቅርታ፣ መነጠልን በመደመር የሻረ ሚዛናዊ የታሪክ አተያይ አዲሱ የፖለቲካ ባሕል ኾኗል።
ኢኮኖሚውም ከግብርና ጥገኝነት ተላቅቆ ማዕድን፣ ቱሪዝም እና ቴክኖሎጂን ወዳቀፈ ባለብዙ ዘርፍ ስትራቴጂ ተሸጋግሯል። በዕዳ ተዳክመው የነበሩ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ኾልዲንግስ ሥር ዳግም ተዋቅረው ከኪሳራ ወደ ትርፋማነት ተሸጋግረዋል።
በቴክኖሎጂ ዘርፍም በዲጂታል መታወቂያ (ፋይዳ)፣ በሰው ሠራሽ አስተውሎት እና በዲጂታል ፋይናንስ ሥርዓቶች ኢትዮጵያን በዓለም ተወዳዳሪ የሚያደርግ ጠንካራ መሠረት ተጥሏል።
የኮሪደር ልማቱ እና የቅርሶች እድሳት ከተሞችን ይበልጥ ለኑሮ፣ ለንግድ እና ለቱሪዝም ማራኪ በማድረግ ግዙፍ የኢኮኖሚ ሞተር አድርጓቸዋል።
የውጭ ጥገኝነትን ሰብሮ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ በበጋ መስኖ እና በሌማት ትሩፋት አመርቂ ውጤት ተመዝግቧል። 56 ቢሊዮን ችግኞችን በተተከሉበት የአረንጓዴ አሻራ ደግሞ የተፈጥሮ ሚዛን እና ዓለም አቀፍ የዲፕሎማሲ ከፍታ ተመዝግቧል።
የሀገሪቱን እምቅ አቅም አውጥቶ ለመጠቀም በተጀመረው የኢትዮጵያ ታምርት ንቅናቄ የማምረት ባሕል እና የማዕድን ዘርፉ መነቃቃት አሳይተዋል።
የገበታ ፕሮጀክቶችም የሀገሪቱን የተፈጥሮ እና የውኃ ሀብት ወደ ግዙፍ ኢኮኖሚያዊ ጥቅም የቀየሩ ስኬታማ ማሳያዎች ናቸው።
የለውጥ እርምጃዎች የሃሳብን ጥልቀት ከተግባር ፍጥነት ጋር በማዋሃድ የሀገሪቱን እምቅ አቅም ያወጡ እና በራሷ የምትተማመን የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት ጽኑ መሠረት የጣሉ ናቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
