“መስፈንጠር እንደ ሴንጋፖር “

9

 

እንደ አውሮፓውያኑ የዘመን ስሌት 1965 ከማሌዢያ በግዳጅ ስትለይ እጅግ ፈታኝ የመክሰም እና የመውደቅ አደጋ የተጋረጠባት አነስተኛ ደሴት ነበረች፡፡

ሠርቶ ለመለወጥ ያግዘኛል የምትለው እና ተስፋ የምታደርገው የተፈጥሮ ሃብት የሌላት ሴንጋፖር በዙሪያዋ የከበቧት ጎረቤቶቿም ስጋት እንጅ ወረት

እንደማይኾኗት ስለምታውቅ ነገሮችን ሁሉ ከሕልውና ፈተና ጋር ከማያያዝ የተሻለ አማራጭ እንደሌለ ገብቷታል፡፡

የአዲስ ጎጆ ወጭዋን ሴንጋፖር የወደፊት አቅጣጫ የመቀየስ ፈታኝ ታሪካዊ ኀላፊነት የወደቀባቸው መሥራች መሪዎቿ በአጭር ታጥቀው እና ወኔ ሰንቀው ሴንጋፖርን ሀገር ማድረግ ግድ እንደሚል አምነዋል፡፡

ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን የው እና የፋይናንስ ሚኒስትሩ ጎ ኬንግ ስዊ (ዶ.ር) የጥንታውያኑን የአቴንስ እና የቬነስ መንግሥታት የለውጥ ጉዞ ተዘዋውረው

ሲመረምሩ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትሩ ኤስ ራጃራትናም ደግሞ የሴንጋፖርን ፈጣን የዕድገት ፍኖተ ካርታ በቢሯቸው ቁጭ ብለው ይነድፋሉ፡፡

የሀገሪቷን መጻዒ እጣ ፈንታ በጥበብ የሚቀርጹት መሪዎቿ የሃብት እጥረት የሚፈትናትን ሴንጋፖር በስትራቴጂካዊ ንግድ እና በዓለማቀፋዊ ቅቡል የተግባቦት ብቃት ለመተካት የሚያስችል አሥተዳደር በአጭር ጊዜ ውስጥ ዘረጉ፡፡

ዛሬ ላይ በዓለም ላይ ባሉ ታዳጊ ሀገራት ፖሊሲ አውጭዎች ዘንድ ልዩ ትኩረትን የሳበው “የሴንጋፖር ሞዴል” መነሻው ሀገሪቷን ከተጋረጠባት የድህነት እና ደኅንነት ናዳ ለመታደግ ያኔ በጥበብ የተቀረጸ መውጫ መንገድ ነበር፡፡

የቤልጂየም ጠቅላይ ሚኒስትር ባርት ደ ቬቨር ሀገራቸው የገጠማትን የምጣኔ ሃብታዊ ውድቀት ለመታደግ “ማከም ወይም ማክሰም” በሚል ርእስ

ያቀረቡት አማራጭ ሃሳብ የተቀዳው ከሴንጋፖር ጠቅላይ ሚኒስትር ሊ ኩዋን የው አራት የኢኮኖሚ መርሆዎች እንደኾነ ይነገራል፡፡

ምንም እንኳን የሴንጋፖር መሪዎች “የሴንጋፖር ሞዴል” ከተለየ ሀገራዊ የሕልውና አውድ የመነጨ በመኾኑ

ሌሎች ሀገራት እንደ ሁለንተናዊ ንድፈ ሃሳብ ቀጥታ ሊተገብሩት አይችልም የሚል ጥንቃቄ አዘል አቋም እያንጸባረቁ ቢኾንም፡፡

የሴንጋፖር ተዓምራዊ የውጥ እና የዕድገት ግስጋሴ ተሞክሮ ለምጣኔ ሃብታዊ ማሻሻያ ብቻ ሳይኾን ለደኅንነት እና ለጂኦ-ፖለቲካል ሕልውናም የተለየ ትምህርት ይሰጣል፡፡

የአትላንቲክ ጦር ቃልኪዳን ቡድን ቀስ በቀስ መሸርሸር እና ተጽዕኖ አልባ መኾን፣ ዓመታትን ያስቆጠረው እና ዛሬም ድረስ መቋጫ ያላገኘው የሩሲያ-ዩክሬን ጦርነት፣

በቅርቡ በእስራኤል እና አሜሪካ ትብብር ከኢራን ጋር የተፈጠረው ግጭት እና የሆርሙዝ ሰርጥ ደግሞ ደጋግሞ መዘጋት የሀገራትን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት

ከአንዱ ወደ ሌላው ሲያላጋው ሴንጋፖር ግን ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነቷን ከብሔራዊ ጥቅሟ አንጻር በመቃኘት ሳይትዋዥቅ እንደቀጠለች ዘልቃለች፡፡

የፊንላንዱ ፕሬዝዳንት አሌክሳንደር ስቱብ አሁን ላይ ያለውን የዓለም አቀፍ ዐውድ እና ሁኔታ የታሪክ ሂደት “ሽግግር” ሲሉት፤ የካናዳው ጠቅላይ ሚኒስትር ማርክ ካርኒ ደግሞ “ስብራት” ሲሉ ገልጸውታል።

የቀድሞው የሴንጋፖር የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጆርጅ የኦ እንደሚሉት በዓለም አቀፍ የደኅንነት ምህዳር ውስጥ አነስተኛ ደሴት የኾነችው ሴንጋፖር የራሷን ሕልውና እንዴት ጠብቃ መዝለቅ እንደቻለች መመርመር ለታዳጊ ሀገራት ወቅታዊ ጥያቄዎች ምላሽ ይሰጣል ይላሉ።

ሴንጋፖር እንደ ኢትዮጵያ ላሉ ለሌሎች ሀገራት ተሞክሮ መኾን የሚችሉ ሦስት ዋና ዋና ስትራቴጂካዊ መርኾዎች አሏት፡፡ የመጀመሪያው ከማንም ጋር ሳይወግኑ የሀገሪቱን ብሔራዊ ጥቅም ብቻ

የሚያስቀድም ሁለገብ ተግባራዊ ወይም ፕራግማቲክ ዲፕሎማሲን መከተል የሚል ነው።

ሁለተኛው ስትራቴጂካዊ መርሆዋ ዓለም አቀፍ ሕግን እና ተቋማትን እንደ ጋሻ በመጠቀም እና ሁለገብ የተጽዕኖ ደረጃን በማሳደግ የሉዓላዊነት እኩልነትን ማስከበር የሚል ነው።

የመጨረሻው አስታራቂ እና አጀንዳ ቀራጭ መኾን የሚል ሲኾን በዚህም ዓለም አቀፍ ውጥረቶችን የሚያስተናግድ ገለልተኛ መድረክ በመኾን የሀገሪቱን ስትራቴጂካዊ ጠቃሚነት ለመጨመር ታስቦ የተቀረፀ እንደኾነ ያሳያሉ።

አሁን ባለንበት ሉላዊ የዓለም መስተጋብር በአንድ ዘርፍ ብቻ ተሽሎ መውጣት አዋጭ አለመኾኑን የሴንጋፖር ተሞክሮ ያሳያል፡፡

ምጣኔ ሃብታዊ ዕድገትን ለማረጋገጥ እና የዜጎችን መሠረታዊ ፍላጎት ለማረጋገጥ አስተማማኝ ደኅንነትን መገንባት፣ ከብሔራዊ ጥቅም የመነጨ ዲፕሎማሲ፣ ድንበር ተሻጋሪ ንግድ፣ ተጽዕኖ ፈጣሪ ሀገር መገንባት እና በቴክኖሎጂ መልማት ከሴንጋፖር የሚወሰዱ ተሞክሮዎች ናቸው፡፡

👉 engelsbergideas.com የመረጃ ምንጫችን ነው።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ! 🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_28_2019_ዓ_ም

✍️ በታዘብ አራጋው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleብልጽግና ፓርቲ የአፍሪካ ፖለቲካ ፓርቲዎች ኢኒሼቲቭን በበላይነት እንዲመራ በሙሉ ድምፅ ተመረጠ።
Next article🌶️ “በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የበርበሬ ምርት ይጠበቃል”