🌶️ “በአማራ ክልል ከ1 ነጥብ 3 ሚሊዮን ኩንታል በላይ የበርበሬ ምርት ይጠበቃል”

6

 

በአማራ ክልል በርበሬ በስፋት ከሚመረትባቸው አካባቢዎች መካከል ማዕከላዊ ጎንደር ዞን አንዱ ነው።

በዞኑ የጣቁሳ ወረዳ ነዋሪው አርሶ አደር አስቀናው ብረሃኑ በርበሬ በስፋት የማምረት የካበተ ልምድ እንዳላቸው ነግረውናል። ብዛት ያለው የበርበሬ ምርት እንደሚሰበስቡም ነው የገለጹት።

ሕይወታቸውም ከበርበሬ እና የቅመማ ቅመም ሰብል ጋር ጥብቅ ቁርኝት እንዳለው ተናግረዋል።

በዚሁ ጠንካራ ሥራቸው ኑሯቸውን በተሻለ ሁኔታ እየመሩ መኾናቸውን ነው ያስረዱት። ዘንድሮም የዝናብ እጥረት የተወሰነ ሥጋት ቢፈጥርባቸውም እንኳ የተሻለ ምርት እየጠበቁ መኾናቸውን ገልጸዋል።

የማዕከላዊ ጎንደር ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ ንጉሤ ማለደ በምርት ዘመኑ በዞኑ 11 ሺህ 250 ሄክታር መሬት በበርበሬ ሰብል የተሸፈነ ነው፤ 202 ሺህ 500 ኩንታል ምርት ይጠበቃል ብለዋል።

የታቀደውን የበርበሬ ምርት ለማሳካት በኩታገጠም ከማልማት ባለፈ የአርሶ አደሮች ሠርቶ ማሳያዎችን በመጠቀም ለአርሶ አደሮች ግንዛቤ መፈጠሩን ገልጸዋል።

ሰብሉ በተሻለ ቁመና ላይ ይገኛል ያሉት ኀላፊው ምርቱ በገበያ ላይ ያለውን የዋጋ መናር ችግር የሚያቃልል ነው ብለዋል።

በአማራ ክልል ግብርና ቢሮ የሆርቲ ካልቸር ልማትና ቴክኖሎጂ ሽግግር ዳይሬክተር አበበ መኮነን በክልሉ በተያዘው የምርት ዘመን ከ85 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በበርበሬ ሰብል መሸፈኑን ተናግረዋል።

ከዚህም ከ1 ሚሊዮን 300 ሺህ ኩንታል በላይ ምርት ለማምረት መታቀዱን ገልጸዋል።

በክልሉ የበርበሬ ሰብል በማዕከላዊ ጎንደር፣ በምዕራብ ጎጃም ዞኖች እና በአዊ ብሔረሰብ አሥተዳደር ስር ባሉ ሰባት ወረዳዎች በስፋት ይመረታል ብለዋል። በዚህም በኩታገጠም ከ46 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት እየለማ እንደኾነ ነው የገለጹት።
​
​ጥሩ የሰብል ቁመና መኖሩንም አንስተዋል። የመጀመሪያው ዙር የበርበሬ ምርት ስብሰባ ሥራ

ተጀምሮ በመከናወን ላይ ነው ያሉት ዳይሬክተሩ ምርቱን በጥራት እና በብዛት ለማግኘትም አስፈላጊው ክትትል እየተደረገ ይገኛል ብለዋል። በዘርፉ ቴክኖሎጂን በአግባቡ በመጠቀም የተሻለ ምርታማነትን ለማስመዝገብ መሠራቱን አንስተዋል።

የበርበሬ ሰብል የአፈር ለምነትን ከማሻሻል ባለፈ የአርሶ አደሮችን ገቢ በማሳደግ የኑሮ ደረጃቸን ለመገንባት ከፍተኛ አስተዋጽኦ አለው ነው ያሉት።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_28_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“መስፈንጠር እንደ ሴንጋፖር “
Next article“ከቀጣይ ጥር ወር ጀምሮ ስምንት የክልሉ ተቋማት ወደ ሪፎርም ትግበራ ይገባሉ”