“ያልተጠቀምንባቸው የፈውስ እንቁዎች”

21
የሰው ልጅ የተለያዩ ሕመሞች ሲያጋጥሙት ለሕመሙ ድኅነት ዘመናዊ እና ባሕላዊ መድኃኒቶችን ሲጠቀም ይስተዋላል። በየአካባቢው የሚገኙ እጽዋትን በመጠቀም በባሕላዊ መንገድ ሕመሙን ሲያስታግስ እና ሲፈውስ ማስተዋልም የተለመደ ነው።
በየአካባቢው የሚገኙ ሀገር በቀል የመድኃኒት እጽዋት ደግሞ የፈውስ ምንጭ ሲኾኑ ይስተዋላል። ሀገር በቀል ችግኞችን በመጠበቅ ከሳይንስ ጋር በማስተሳሰር ፍቱን መድኃኒት ማድረግ ደግሞ ከትምህርት ተቋማት የሚጠበቅ ጉልህ ሚና ነው።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ ሀገር በቀል ችግኞችን በመጠበቅ ከሳይንስ ጋር ለማስተሳሰር እየሠራ ይገኛል። በዩኒቨርሲቲው የተፈጥሮ ሃብት አያያዝ ትምህርት ክፍል መምህር፣ ተመራማሪ እና የዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል
💊
የመድኃኒታማ እጽዋት ማዕከል አሥተባባሪ ፈቃዱ ጥሩነህ በማዕከሉ 341 ለመድኃኒት የሚያገለግሉ ሀገር በቀል እጽዋት መኖራቸውን ገልጸዋል። ዝርያዎችን የማሠባሠብ ሥራ በትኩረት መከናወኑን ነው ያነሱት።
ማዕከሉ ትላልቅ ዛፎችን፤ ቁጥቋጦዎችን፤ የሀረግ እና የቅመማ ቅመም እጽዋትን በአራት ዘርፎች በመለየት የማልማት ሥራ እያከናወነ ነው።
👉 የማዕከሉ መቋቋም ምን ጠቀሜታ አለው?
🍀 ለመማር ማስተማር እና ለምርምር ያገለግላል።
🍀 ሀገር በቀል እጽዋት እንዳይጠፉ፤ ዝርያቸው እንዲጠበቅ እና እንዲሰፋ ያስችላል።
🍀 ለመድኃኒት ቅመማ ያገለግላል💊።
🍀 ተማሪዎች የእጽዋትን ባሕሪ እንዲረዱ በተግባር ዕውቀትን እንዲቀስሙ ያስችላል ብለዋል። የእጽዋት መጠበቅ ለአየር ንብረት፤ ለኢኮኖሚያዊ እና ለማኅበራዊ ጉዳዮች ጠቀሜታቸው የጎላ ነው ብለዋል። የሀገር በቀል የመድኃኒት እጽዋት ማኅበረሰቡ በባሕላዊ መንገድ እንደሚጠቀማቸው ያነሱት ተመራማሪው ከሳይንስ ጋር በማስተሳሰር ጥቅም እና ጉዳታቸውን በመለየት ፍቱን እንዲኾኑ ይሠራል ነው ያሉት።
የሀገር በቀል እጽዋት መጥፋት የአየር ንብረት እንዲዛባ፤ ድርቅ እና ርሃብ እንዲከሰት ያደርጋል ብለዋል። የሀገር በቀል እጽዋት ያልተጠቀምንባቸው እንቁዎች ናቸው ነው ያሉት።
የሀገር በቀል ችግኞችን በስፋት በመትከል ምንጮች እንዲጎለብቱ፤ የመድኃኒት ምንጭ እንዲኾኑ፤ ምርት እና ምርታማነት እንዲጨምር፤ የኢኮኖሚ ስኬት እንዲመዘገብ ምቹ ሥነ ምኅዳር እንዲፈጠር ሁሉም የድርሻውን ሊወጣ ይገባል ብለዋል።
የእንጅባራ ዩኒቨርሲቲ የምርምር እና ማኅበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዝዳንት ክንዴ ብርሃን (ዶ.ር) ዩኒቨርሲቲው ሀገር በቀል የመድኀኒት እጽዋትን በሳይንሳዊ ምርምር በማስደገፍ የተለያዩ በሽታዎችን መፈወስ የሚያስችሉ ዘመናዊ መድኃኒቶችን ለመቀመም ግብ ይዞ እየተሠራ ነው ብለዋል።
ባለሙያዎች በዘርፉ ምርምር እንዲሠሩ ዩኒቨርሲቲው ምቹ ኹኔታን እየፈጠረ መኾኑን ተናግረዋል። በሕክምና ኢንዱስትሪው ሀገር በቀል ዕውቀት የራሱን አስተዋጽኦ እንዲያሳርፍ በትኩረት እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡ እጽዋትን ዋጋ ሰጥቶ መጠበቅ እንዳለበትም ገልጸዋል።
ዘጋቢ፦ ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን የአሥፈጻሚ አካላት አደረጃጀት አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።
Next articleከአስተሳሰብ ለውጥ እስከ መሬት የወረደ ሀገራዊ ስኬት።