የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አዲሱን የአሥፈጻሚ አካላት አደረጃጀት አዋጅ በሙሉ ድምጽ አጸደቀ።

38
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የፌዴራል መንግሥት አሥፈጻሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅን መርምሮ በሙሉ ድምጽ አጽድቋል፡፡
ምክር ቤቱ ረቂቅ አዋጁን ዛሬ ባካሄደው 1ኛ ዓመት የሥራ ዘመን 1ኛ ልዩ ስብሰባው ነው ያጸደቀው፡፡ የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አባል እና የመንግሥት ተወካይ ፍቃዱ ተሰማ ግልጽ እና ውጤታማ የኾነ የአሥፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት በመፍጠር የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና የተጠሪ ተቋማት የውልና የተናጠል ተግባር በግልጽ በማስቀመጥ ረገድ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መኾኑን አስረድተዋል፡፡
የረቂቅ አዋጁን አስፈላጊነት እና ዓላማ በተመለከተ አስረጂ ኾነው የቀረቡት የመንግሥት የሥራ ኀላፊዎች ፍጹም አሰፋ (ዶ.ር) እና ሃና አርዓያሥላሴ በዝርዝር ሪፖርት ለምክር ቤቱ አቅርበዋል፡፡
በመንግሥት አሥፈጻሚ ተቋማት መሥሪያ ቤቶች ባለፉት አምስት ዓመታት ውስጥ የታዩትን ውስንነቶች ለመቅረፍ ረቂቅ አዋጁ እንደሚያግዝ አንስተዋል። የዜጎችን ሰብዓዊ እና ዴሞክራሲያዊ መብቶች እንዲከበሩ እና የሕዝቡ የኑሮ ደረጃን ለማሻሻል እና የአገልግሎት ዘርፉን ለማሳለጥ እንደሚያግዝም አንስተዋል።
ረቂቅ አዋጁ ሰፊ ጥናት የተደረገበት እና ከሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች እና ከተጠሪ ተቋማት ጋር ውይይት በማድረግ በቂ ግብዓት ማግኘት መቻሉን አስረድተዋል፡፡
የተቋማትን አደረጃጀት በግልጽ ማስቀመጥ የሥራ ኀላፊዎች የመንግሥት እና የሕዝብን ሃብት በአግባቡ እንዲጠቀሙ ለማስቻል ረቂቅ አዋጁ ትልቅ አቅም እንደሚፈጥር አስረድተዋል፡፡
የምክር ቤት አባላት በበኩላቸው አንዳንድ ተጠሪ ተቋማት ለወጥ በደንብ የሥራ ባህሪያቸውን እና ያላቸውን ፋይዳ ያገናዘበ መኾን እንዳለበት አስገንዝበዋል፡፡
ቀልጣፋ እና ውጤታማ አደረጃጀት በመፍጠር የተቋማትን የማሥፈጸም አቅምን ለማሳደግ ረቂቅ አዋጁ ሚናው የጎላ መኾኑን ገልጸዋል፡፡
ምክር ቤቱ ባካሄደው ልዩ ስብሰባው የፌዴራል መንግሥት አሥፈጻሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የቀረበ ረቂቅ አዋጅ፤ አዋጅ ቁጥር 1440/2019 አድርጎ በሙሉ ድምጽ መጽደቁን ከሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የተገኘው መረጃ ያመለክታል፡፡
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleከጠባቡ ኩሬ ወደ ሰፊው ዓለም:- የኢትዮጵያ ማንነት እና የታላቅ ሥልጣኔ ርዕይ
Next article“ያልተጠቀምንባቸው የፈውስ እንቁዎች”