
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) “የኢትዮጵያ ዘላቂ ችግር የሚፈታው ኢትዮጵያ ሥልጣኔ ስትገነባ ብቻ ነው” ያሉት ሀሳብ ሀገሪቱ ለዘመናት ከተዘፈቀችበት አዙሪት ለመውጣት የሚያስችላትን ስትራቴጂካዊ አቅጣጫ የሚያመላክት ነው።
የዛሬው ትውልድ አደራ እና የነገው ማኅተም የኾነው ይህ የሥልጣኔ ስንቅ የፖለቲካ ንትርኮች፣ የድህነት አረንቋ እና የማንነት ግጭቶች ጊዜያዊ በኾኑ ማስታገሻዎች እንደማይፈቱ የሚነግር ነው።
ሥር-ነቀል የኾነ ተቋማዊ፣ ቴክኖሎጂያዊ እና አዕምሯዊ ሽግግርን ለማምጣት የዘመናት ሀገራዊ ሕመማችንን እስከወዲያኛው የሚፈታ እውነተኛ እና አዲስ ኢትዮጵያዊ ሥልጣኔን መገንባት ይጠይቃል ብለዋል።
እውነተኛ ሥልጣኔ ደግሞ ከግዙፍ የመሠረተ ልማት አውታሮች ግንባታ ባለፈ የፖለቲካ ባሕልን ማዘመን ነው። ኢትዮጵያ አሁን ካለችበት ተደጋጋሚ የፖለቲካ ቀውስ አዙሪት መውጣት የምትችለው ነፍጥን እንደ ብቸኛ አማራጭ በመውሰድ ሳይኾን ይልቁንም በሠለጠነ መንገድ በውይይት እና በድርድር ብቻ እንጂ።
ልዩነቶችን በጠመንጃ አፈሙዝ ሳይኾን በጠረጴዛ ዙሪያ መፍታት የሠለጠነ ማኅበረሰብ ከፍተኛው መገለጫ እና ለዘላቂ ሰላም የማይተካ ቁልፍ መሳሪያ ነው። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ጥንትም ችግሮቿን በንግግር እንደምትፈታ በሚያመላክት መንገድ አሁንም ለታጣቂ ኀይሎች የሰላም ጥሪ አቅርበዋል።
ከዕለታዊ የጥላቻ እና የጠመንጃ ፖለቲካ ጫጫታ ወጥቶ ልዩነቶችን በንግግር እየፈቱ አብሮ የመሥራት እሴትን ማዳበር፣ ለዛሬዋ ኢትዮጵያ የቅንጦት ሳይኾን ብቸኛው የሕልውና እና የዘላቂ መፍትሔ መንገድ ነው።
ሰላማዊ መንገድን የመከተል ይህ የሰላም ባሕል ሀገሪቱን ከታሪካዊ የድህነት ትርክት ከሚያወጡት ታላላቅ ሀገራዊ ፕሮጀክቶች ጋር ሲዋሃድ ደግሞ ሀገሪቱ ዘላቂ የችግር መፍቻ ቁልፏን በተጨባጭ ትጨብጣለች።
ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ወድማ የነበረችው ደቡብ ኮሪያ እና በውስጥ ግጭት ትማቀቅ የነበረችው ሲንጋፖር አሁን ላሉበት ከፍታ የበቁት የጠመንጃ ሽኩቻን ትተው የብቃት፣ የትምህርት እና የቴክኖሎጂ ሥልጣኔን በመገንባታቸው ነው።
በኢትዮጵያም አሁን የተጀመሩትን የጉባ ብሥራቶች ጨምሮ የታላቁ ሕዳሴ ግድብ፣ የግብርና እና የኮሪደር ልማቶች፣ የቱሪዝም የመስህብ ሀብቶችን የማስፋት እና የዲጂታል ሥርዓት ግንባታዎች እና ሌሎች ግዙፍ ፕሮጀክቶች የዚህ አዲስ ሥልጣኔ ምሰሶዎች ናቸው።
ታላቁን ሀገራዊ ርዕይ ከዳር ለማድረስ ግን ትኩረት የሚሹ ጉዳዮች መኖራቸውን ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ይናገራሉ። ቀዳሚው በሰፈር እና በመንደር ጠባብ ኩሬ ውስጥ ከመዋኘት ወጥቶ ወደ ግዙፉ የዓለም መድረክ ከፍ ብሎ መውጣትን ማሰብ ይገባል ነው ያሉት።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
