🇪🇹 ከቁጭት ወደ ሥልጣኔ – የመደመር መንግሥት እሳቤ።

14

 

ኢትዮጵያ ሺህ ዘመናትን ያስቆጠረ የመንግሥት አሥተዳደር ታሪክ ያላት እና ለዓለም የዲፕሎማሲ እንዲሁም የሥልጣኔ እሴቶችን ካስተዋወቁ ቀደምት ሀገራት አንዷ ናት።

በዚህ ረጅም ታሪኳ ውስጥ ለገጠሟት ሁለገብ ተግዳሮቶች መፍትሔ ለመስጠት እና የሀገረ መንግሥት ግንባታ ሂደቷን ለማጠናከር የመደመር እሳቤ ትልቅ የፖለቲካ ፍልስፍና ማዕቀፍ ኾኖ አገልግሏል።

መደመር ጽኑ እና ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ሀሳብን፣ ሰውን፣ ሀብትን እና ተቋማትን በማቀናጀት ከነበሩት ስህተቶች እና ከፀረ ዴሞክራሲያዊ አካሄዶች መማርን የሚጠይቅ ሀገራዊ አቅጣጫ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደገለጹት የኢትዮጵያ የለውጥ ጉዞ፣ የቁጭት እና የሀገር በቀል ሥርዓት ግንባታ አስፈላጊነት በጥልቀት መዳሰስ አለበት።

የሀገራችን የለውጥ ጉዞዎች ሁልጊዜም ከቁጭት የሚነሱ መኾናቸውን ያስረዱት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ሀገር ወደኋላ ስትቀር እና ዓለም ወደፊት ሲራመድ የሚፈጠር ቁጭት ለለውጥ ትክክለኛ መነሻ እንደኾነ አንስተዋል።

ነገር ግን ቁጭት መነሻ እንጂ መዳረሻ ሊኾን አይችልም። መዳረሻው ጠንካራ ሥርዓት፣ ማጠቃለያው ደግሞ ዘላቂ ሥልጣኔ ነው።

ጠንካራ ሥርዓት ደግሞ በአንድ ጀምበር የሚገነባ ሳይኾን ትዕግሥትን፣ ስክነትን፣ ጥበብን እና ተከታታይ ጥረትን የሚጠይቅ ሂደት ነው።

ኢትዮጵያውያን በታሪካቸው በአንድነት ተሳስረው፣ ተዋልደው እና ተጋምደው፣ ችግሮቻቸውን በውይይት እና በዕርቅ ፈተው ኖረዋል።

ዳር ድንበራቸውን በአንድነት ተመው በደም እና በአጥንታቸው ያስከበሩት፣ ክፉ እና ደጉን ዘመን በአብሮነት ያሳለፉት በመደመር እሳቤ ስለተጋመዱ ነው።

ፈተናዎች ያልበገሩት፣ ችግሮች ያልተበጠሱት፣ የባዕድ ርዕዮተ ዓለሞች ያልቀየሩት እና የፖለቲካ ሊሂቃን ያልከፋፈሉት ኢትዮጵያዊነት ሊጸና የቻለውም በዚህ በመደመር መንገድ በመጓዛችን ነው ብለዋል።

ባለፉት ዘመናት የነበሩ መሪዎች ከሚያዋጣው የሀገር ውስጥ መንገድ ይልቅ አቋራጭ በመምረጥ ከባሕር ማዶ የተቀዱ ርዕዮተ ዓለሞችን በግድ በኢትዮጵያ መሬት ላይ ለመትከል ሲሞክሩ ቆይተዋል።

መሬቱን ለዘሩ ወይም ዘሩን ለመሬቱ ማስተካከል ባለመቻሉ አዝመራው አረም እያበቀለ ሀገሪቱ ለከፋ ችግር ስትዳረግ ኖራለችም ባይ ናቸው።

ከሥሩ የተነጠለ ዛፍ እና ከምንጩ የተቆረጠ ወንዝ እንደሚደርቅ ሁሉ ሀገራዊ መሠረቱን ጥሎ የሚጀመር የሥልጣኔ ጉዞም ሩቅ ሊሄድ አይችልም ነው ያሉት።

ስለኾነም የመደመር እሳቤ የበለጸገች አዲሲቷን ኢትዮጵያ ለመገንባት እንደ ሀገራዊ የማሰብያ ቋንቋ ያገለግላል።

ባለፉት ስምንት ዓመታት በተደረጉ ጥናቶች እና ፍተሻዎች ኢትዮጵያ የራሷ የኾነ የታሪክ እና የጥበብ ሀብት እንዳላት የተረጋገጠ ሲኾን ይህም የመደመር እሳቤ ዋና መሠረት ነው ብለዋል።

ኢትዮጵያውያን በታሪክ ዘመናት ሁሉ ብዝኀነትን ከአንድነት፣ የእምነት ልዩነትን ከእሴት ትስስር፣ የግል ፍላጎትን ደግሞ ከጋራ ጥቅም ጋር ደምረው በመጓዝ አብሮነታቸውን አስጠብቀዋል።

አውሮፓውያን እና እስያውያን የራሳቸውን ባሕል እና ፍልስፍና መሠረት አድርገው ሥልጣኔያቸውን እንደገነቡት ሁሉ ኢትዮጵያም ያላትን የሥልጣኔ ሀብት በማዘመን በሀገር በቀል እሳቤ ላይ የታነጸ ጠንካራ ሥልጣኔ መገንባት እንደምትችል አሳይታለች ነው ያሉት።

በታሪኳ ለዓለም ያበረከተችው የመንግሥት አሥተዳደር እና የነፃነት ተምሳሌትነት ዛሬ ላይ የገጠሟትን የዴሞክራሲ፣ የሰላም እና የልማት ጥያቄዎች ለመመለስ በመደመር እሳቤ ያለፉትን ጉድለቶች እያረመች ወደፊት በጋራ ለመጓዝ የሚያስችል ሁለገብ መንገድ በመከተል ላይ እንደምትገኝም ጠቁመዋል።

ሀገራችን የመደመር እሳቤን በተግባር በመተርጎም ታሪካዊ አሸናፊነቷን አስጠብቃ የብልጽግና ጉዞዋን እያረጋገጠች ትገኛለች፤ የብዝኀነት ውብ እሴቶቿን በማጠናከርም ዓለም አቀፍ ተወዳዳሪነቷን እያሳደገች ነውም ብለዋል።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መስከረም_27_2019_ዓ_ም

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleአቶ ታምራት ደምሴ የወልድያ ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ኾነው ተሾሙ።
Next articleከጠባቡ ኩሬ ወደ ሰፊው ዓለም:- የኢትዮጵያ ማንነት እና የታላቅ ሥልጣኔ ርዕይ