
ቀይ ባሕር እና የኤደን ባሕረ-ሰላጤ በዓለም አቀፍ የፖለቲካ፣ የኢኮኖሚ እና የደኅንነት ጉዳይ ላይ ወሳኝ ከኾኑ የውኃ አካላት መካከል ከቀዳሚዎቹ ይጠቀሳሉ። ቀጣናው በዓለም አቀፍ የንግድ እንቅስቃሴ ላይ ከፍተኛ ተፅዕኖ አለው።
የዓለም አቀፍ የነዳጅ ንግድ፣ የተፈጥሮ ጋዝ እና የኮንቴነር መርከቦች ከፋርስ ባሕረ ሰላጤ እና ከእስያ ወደ አውሮፓ እና አሜሪካ የሚጓጓዙበት ዋነኛ መስመር በመኾኑ የዓለም ኢኮኖሚ የጀርባ አጥንት ተደርጎ ይወሰዳል።
የዓለም ታላላቅ ሀገራት ሳይቀር ብሔራዊ ጥቅማቸውን ለማስጠበቅ የጦር ሰፈራቸውን በአካባቢው ገንብተዋል። የኀይል ሚዛን የበላይነትን ለማረጋገጥ የሚፎካከሩበት ወሳኝ ስትራቴጂያዊ አካባቢም ነው።
ኢትዮጵያ በዚህ አካባቢ የምትገኝ በመኾኗ በቀይ ባሕር እና በኤደን ባሕረ ሰላጤ ቀጣና ላይ የነበራት የፖለቲካ እና የንግድ የበላይነት ጥንታዊ እና ጥልቅ መሠረት ያለው ነው።
ለአብነትም በአክሱም ሥልጣኔ ዘመን የአዱሊስ ወደብን ትጠቀም ነበር። በዚህም በግሪክ፣ በሕንድ እና በሮም ሀገራት መካከል ይደረግ የነበረውን የንግድ ልውውጥ በበላይነት በኢትዮጵያውያን ይመራ እንደነበር በታሪክ ተከትቧል።
ኢትዮጵያ በቀጣናው ያላት ፍላጎት የታሪክ ውርስ ብቻ አይደለም። ይልቁንም የሀገሪቱ የወደፊት ሕልውና፣ የኢኮኖሚ ዕድገት እና በቀጣናው ሰላም አስከባሪነትን መሠረት ያደረገ ነው።
ከ130 ሚሊዮን በላይ ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ያለ አስተማማኝ የባሕር በር አማራጭ ዕድገቷን ዘላቂ ማድረግ አይታሰብም። ለዚህም ነው በቀጣናው የባሕር በር ለኢትዮጵያ የሕልውና ጉዳይ ነው የሚባለው።
በቀጣናው ያላትን ታሪካዊ እና ስትራቴጂካዊ ፍላጎት ለማስጠበቅ ባለብዙ ዘርፍ እንቅስቃሴዎችን በማድረግ ላይ ትገኛለች። ለዚህም ከጎረቤት ሀገራት ጋር የጋራ የኢኮኖሚ ትስስር መፍጠርን ቀዳሚ ምርጫዋ አድርጋለች።
በትብብር መልማት ላይ የተመሠረተ የዲፕሎማሲ አቅጣጫንም እየተከተለች ነው። የባሕር ኀይል እንደገና የማደራጀት እና የመከላከያ ኀይሏን የማጠናከር ሥራዎች እየተከናወኑም ይገኛሉ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ(ዶ.ር) እንደተናገሩት ምሥራቅ አፍሪካ፣ ቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስ በሚገናኙበት ልዩ ስፍራ ላይ መገኘት ፈተናም ዕድልም አለው። በዚህ ቀጣና የሚነሳ የለውጥ ዝናብም ኢትዮጵያን ሳይነካ እንደማያልፍ ተናግረዋል።
በተዘጋጀንባቸው በቀደሙት ዘመናት ከቀይ ባሕር እስከ ሕንድ ውቅያኖስ፣ ከሜዲትራኒያን እስከ አትላንቲክ ተጉዘናል፤ ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብናል ብለዋል።
በማዕበል በምትናጥ ዓለም ውስጥ ለመጓዝ መዘጋጀት እንደሚያስፈልግ አስገንዝበዋል። ኢትዮጵያ በመብረቁ ሳትሸበር፣ በነጎድጓዱ ሳትበረግግ፣ በዝናቡ ዶፍ ሳትናጥ በማዕበሉ ከፍ ብላ እንድትቀዝፍ ለማድረግ ከሁሉም እንደሚጠበቅ አስገንዝበዋል።
የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ያለ ባሕር በር ዕውን ሊኾን አይችልም ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ ኢትዮጵያ ወጥቶ መግቢያ በር እንዲኖራት ተግተን እንሠራለን ብለዋል።
የቀይ ባሕር የቀደመ ባለቤትነቷን ዕውን በማድረግ በቀጣናው ተጽዕኖ ፈጣሪነቷን እና መሪነቷን እንደምታረጋግጥም አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
