የዓለም አቀፉ ጂኦፖለቲካ አዲስ አሰላለፍ እና የኢትዮጵያ ስትራቴጂካዊ አቋም።

16
🌍
ዓለም አቀፉ የፖለቲካ ምሕዳር ከሁለተኛው የዓለም ጦርነት በኋላ ታይቶ በማይታወቅ ፍጥነት እየተለወጠ ይገኛል። የኀይል ሚዛኑ ከአንድ ወገን የበላይነት ወደ ብዙ ተዋናዮች የሚሳተፉበት አዲስ የዓለም አሰላለፍ እየተሸጋገረ ባለበት በዚህ ወቅት ኢትዮጵያ ደግሞ በጂኦ ፖለቲካው መሐል ውስጥ ትገኛለች።
የዓለም አቀፍ ግንኙነቶችን እና የውጭ ፖሊሲ ጉዳዮችን የሚዳስሰው የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መረጃ የምዕራባውያን እና የምሥራቃውያን የኀይል ሽግግር አንዱ የዓለም አዲሱ የጂኦፖለቲካ አሰላለፍ እንደኾነ ገልጿል።
ዓለም አቀፉ ምጣኔ ሀብት እና ፖለቲካ በኀያላን ሀገራት መካከል ለሁለት እየተከፈለ ይገኛል። ቻይና እና ሩሲያን የያዘው የብሪክስ ኅብረት አባላቱን በማስፋት የዶላር የበላይነትን እና የምዕራባውያንን ተፅዕኖ ለመቀነስ እየሠራ ነው። ምዕራባውያን በበኩላቸው በቡድን ሰባት እና በሰሜን አትላንቲክ የጦር ቃል ኪዳን ድርጅት (ኔቶ) በኩል የበላይነታቸውን ለማስጠበቅ እየታገሉ ነው ብሏል።
የቀይ ባሕር እና ቀጣናው ስትራቴጂካዊ ውጥረትም ሌላው አሰላለፍ ነው። የዓለም አቀፍ የንግድ መስመር የኾነው ቀይ ባሕር እና ቀጣናው የዓለም ታላላቅ ኀይሎች (አሜሪካ፣ ቻይና፣ ፈረንሳይ) እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት (ሳዑዲ ዓረቢያ፣ የተባበሩት ዓረብ ኤምሬትስ) ወታደራዊ እና ኢኮኖሚያዊ የፉክክር ማዕከል እንደኾነም ዓለም አቀፍ የቀውስ አስወጋጅ ቡድን መረጃ ያመላክታል።
የኢትዮጵያ የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ጽሕፈት ቤት እና የደኅንነት ጥናቶች ኢንስቲትዩት መረጃዎች እንደሚያመላክቱት ደግሞ ኢትዮጵያ የብሪክስ ኅብረት ሙሉ አባል መኾኗ ከቻይና፣ ሩሲያ፣ ሕንድ እና የመካከለኛው ምሥራቅ ሀገራት ጋር ያላትን የኢኮኖሚ እና ስትራቴጂካዊ ትስስር አጠናክሮታል።
በተመሳሳይ ወቅት ግን ከምዕራባውያን አጋሮች ጋር ያላትን የቆየ ግንኙነት ሳታቋርጥ ሚዛናዊ የውጭ ፖሊሲን እየተከተለች ትገኛለች።
የኢትዮጵያ መንግሥት ፈጣን የሕዝብ ቁጥር እና የኢኮኖሚ ዕድገትን ታሳቢ ያደረገ ዘላቂ የባሕር በር የማግኘት ፍላጎት በይፋ ማንሳቱ በኅብረተሰቡ እና በጎረቤት ሀገራት ዘንድ ትልቅ የጂኦ ፖለቲካ ውይይት ፈጥሯል። አቋሟም በሰላማዊ እና ሕጋዊ መንገድ የጋራ ልማትን ማዕከል ያደረገ ነው።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታ መጠናቀቅ እና የኀይል ማመንጨት ምዕራፍ ኢትዮጵያን በምሥራቅ አፍሪካ የኀይል እና የኢኮኖሚ ማዕከል እንዳደረጋትም የዓለም ባንክ መረጃ ያመላክታል።
ኢትዮጵያ የተፈጥሮ ሀብቷን በፍትሐዊነት የመጠቀም ሉዓላዊ መብቷን ያስከበረችበት አቋሟ ተጠናክሮ ቀጥሏል። በጥቅሉ መረጃዎች እንደሚያመላክቱት በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ጂኦፖለቲካ ውስጥ ገለልተኛ ኾኖ ከመቀመጥ ይልቅ የራሷን ብሔራዊ ጥቅም ለማስከበር ከምሥራቅም ከምዕራብም ጋር በጥበብ የመደራደር እና ሚዛኗን የመጠበቅ አካሄድ እየተከተለች ትገኛለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር የመንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር ዓለም አቀፍ እና ጂኦፖለቲካዊ ሁነቶችን ሲያብራሩ ይህንኑ መረጃ አጠናክረዋል። ዛሬ ዘመኑ ተቀይሯል ነገሮች እንደወረዱ አይደሉም ነው ያሉት። ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በፍጥነት ይለዋወጣሉም ብለዋል።
ከሁለቱ የዓለም ጦርነቶች ወዲህ የዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መልኮች በፈጣን ለውጥ ውስጥ እንደሚገኙም ገልጸዋል። የከርሰ ምድር እንቅስቃሴ ምድሪቱን እየናጠ ሜዳውን ተራራ፣ ኮረብታውን ሸለቆ ፣ ባሕሩን ወደ ውቅያኖስ እየለዋወጠ አዲስ ቅርጽ እና መልክ ያስይዛታል። በተመሳሳይ መልኩ ዓለምም በጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቿ ምክንያት መልክ እና ጠባይዋ ተቀያይሯል ነው ያሉት።
አይገመቴነት የዘመን ዋነኛ መገለጫ እየኾነ ነው፤ ቋሚ አሰላለፍ ማየት ብርቅ ኾኗል። የባለብዙ ዋልታ ዓለም ሊወለድ በሚታገልበት በዚህ ወቅት ጎራ መርጦ ማን ይቆማል? ማንም! ሲሉም ተደምጠዋል።
የትኛው ፖለቲካዊ እሳቤ በዓለም ላይ እንደሚነግስ ከግምት በዘለለ በእርግጠኝነት ማን መናገር ይችላል? ማንም! ምን ዓይነት የኢኮኖሚ አካሄድ የቀጣይ ዓለም ሥርዓት እንደሚኾንስ በውል ተለይቷል? በፍጹም! ጥቁርና ነጩ ያልለየለት ግራጫ የፖለቲካ እና የኢኮኖሚ አውድ ውስጥ እንገኛለን ነው ያሉት።
ታሪክ ወደየትኛው አዲስ ምዕራፍ እንደሚያደርሰን በግልጽ በማይታወቅበት መንታ መንገድ ላይ መኾናችን እሙን ነው። ለሀገር የሚበጀውን መንገድ መርጦ መከተል የዚህ ትውልድ ታላቁ አደራ ይኾናል ብለዋል።
✍️ዘጋቢ፦ ሮዛ የሻነህ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleቀይ ባሕር ለኢትዮጵያ፤ የዛሬ ሕልውና፣ የነገ ተስፋ።
Next article‎ከነፍጥ አዙሪት ወደ ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድ- የኢትዮጵያ ጉዞ