
ኢትዮጵያ በዘመናት ታሪኳ በተለያዩ ሥርወ መንግሥታት ተዳድራለች። በታሪኳ በየወቅቱ የሚመጡ መንግሥታት የራሳቸውን የፖለቲካ ርዕዮት አራምደዋል። ዘመናዊ የኢትዮጵያ ሥልጣኔ ከዘመነ መሳፍንት ማክተም እና ከአጼ ቴዎድሮስ መምጣት ጀምሮ መሠረቱ እንደተጣለ የታሪክ መዛግብት ያሥረዳሉ።
የኢትዮጵያ የመንግሥታት ለውጥ ታሪክ በጦርነት አዙሪት የተቃኘ ይመስል የመንግሥታት ሥርዓት ሲወድቅ እና ሲነሳ በጦርነት የታጀበ መኾኑን የታሪክ መዛግብት በልኩ አስቀምጠውታል።
ከዘውዳዊ አገዛዝ ወደ ወታደራዊ ሥርዓት ሲሸጋገር፤ ከወታደራዊ ሥርዓት ወደ ዴሞክራሲያዊ መርኅ ሲቀየር የመንግሥትን ሥርዓት በኀይል በመናድ ላይ የተመሠረተ መኾኑ የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው። በኀይል የመንግሥት ሥርዓትን ማፍረስ ዘመኑን የማይዋጅ የኋላ ቀር ጉዞ መኾኑ ለጥያቄ የማይቀርብ ጉዳይ ነው።
የዓለም የፖለቲካ መድረክ መከባበርን፣ ብሔራዊ ጥቅምን፣ የሃሳብ የበላይነትን፣ የሕዝብ ድምጽን እና ሌሎች አይነኬ ተግባራትን አስቀድሟል።
በኢትዮጵያም ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድን ለማስኬድ ሙከራዎች ተደርገዋል። ሕዝቡ የሚያሥተዳድረውን መንግሥት በምርጫ ሂደት በመምረጥ ዘመናዊ የፖለቲካ ሥርዓት መከተል ከጀመረ ውሎ አድሯል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ከሰሞኑ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ባደረጉት ንግግር ዓለም ቀዳሚውን የኢንዱስትሪ አብዮት ሲያካሂድ እኛ በዘመነ መሳፍንት ሹክቻ ውስጥ ነበርን፤ የእርስ በእርስ ግጭቱ ብዙ ነገሮችን አሳጣቶናል ብለዋል።
ሥርዓት የሁሉም ነገር መሠረት መኾኑን ሲገልጹም ቁጭት መነሻ እንጂ ማድረሻም መዳረሻም አይኾንም፤ ማድረሻው ሥርዓት ሲኾን መዳረሻው ደግሞ ሥልጣኔ መኾኑን ገልጸዋል።
በትውልድ ቅብብሎሽ የደለበውን ፖለቲካዊ እና ማኅበራዊ ወረት ፈልፍለን፣ ከባሕር ማዶ የምናገኛቸውን ጠቃሚ ጥበቦች ከኢትዮጵያዊ እሳቤ ጋር እንዲጣጣሙ አድርገን፣ በጎደለ ሞልተን ጠንካራ ሥልጣኔ መገንባት እንችላለን ነው ያሉት።
በማክሮ ኢኮኖሚ፣ በጸጥታ ዘርፍ፣ በአምራች ኢንዱስትሪ፣ በግብርና፣ በትምህርት፣ በጤና፣ በኢነርጂ፣ በመሠረተ ልማት አፈጻጸም፣ በውጭ ግንኙነት እና በሌሎች ዘርፎች የተጀመሩ ሪፎርሞች ፍሬ ማፍራት መጀመራቸውንም ነው ያነሱት።
ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድ ለኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቅኔ ጭምር ተነጋግረን የምንግባባ ሕዝቦች ሃሳብን በጠመንጃ፣ ፍላጎትን በሽፍትነት ለመግለጽ ዛሬም ይዳዳናል ነው ያሉት። በመደመር መንግሥት ለብሔራዊ ጥቅም በጋራ መሥራት እንደሚቻል በተግባር አሳይተናልም ብለዋል።
ዴሞክራሲያዊ የፖለቲካ ምሕዳር በሕገ መንግሥታዊ ሥርዓት ላይ አጽንተን የኢትዮጵያን ሕልሞች እናሳካለን፤ የበለጸገች ኢትዮጵያን እናወርሳለን። የፖለቲካ ምሕዳራችን በትብብር እና በፉክክር ሚዛን ላይ ተመስርቶ እንዲቀጥል ይደረጋል ሲሉም ሰላማዊ የፖለቲካ ልምምድን ለማስቀጠል እንደሚሠራ ገልጸዋል።
የኢፌዴሪ ፕሬዝዳንት ታዬ አጽቀሥላሴ ከሰሞኑ የኢትዮጵያን የፖለቲካ ልምምድ ለማዘመን እና የሰከነ የፖለቲካ ተራግቦት እንዲኖር መንግሥት መሥራቱን ተናግረዋል።
የጠብመንጃ ባሕልን እና የነፍጥ አዙሪትን በዘላቂነት በማስቀረት፤ የሀገራችን የተለምዶ የፖለቲካ ማጠንጠኛ ውርስ ከኾነው የአምባጓሮ፣ የአመጽ እና የግጭት ጎዳና በዘላቂነት ለመላቀቅ የፖለቲካ ልምምዳችን በሰላም፣ በንግግር፣ በዕውቀት እና በመደማመጥ ላይ እንዲመሠረት መንግሥት ከፍ ያለ ሥራ እና ትኩረት የሚሰጠው ይኾናል ነው ያሉት።
በየዘመኑ ሲንከባለል የመጣው የአመጻ የፖለቲካ ተግባር የሚያከትምበት፤ የልማት እና የሰላም ድምጽ እንቢልታ የሚናኝበት ጊዜ ላይ ደርሰናልም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ያየህ ፈንቴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
