
ኢትዮጵያ በዓለም መድረክ የራሷ የኾነ ደማቅ ሥልጣኔ እና የረጅም ዘመናት የሥነ መንግሥት ታሪክ ያላት አንጋፋ ሀገር ናት። ነገር ግን ሥልጣኔዋን እና ዕድገቷን በዐይነ ቁራኛ የሚከታተሏት ብዙዎች በመኾናቸው ይህ የረጅም ዘመናት ጉዞዋ አልጋ በአልጋ አልነበረም። አንድ ጊዜ ወደፊት ሁለት ጊዜ ወደኋላ የኾነ የመንገዳገድ ጉዞ ስታደርግ ቆይታለች።
የፖለቲካ ሳይንስ ምሁራን እንደሚጠቅሱት ከፍተኛ የውጭ ኀይላት ጣልቃ ገብነት፣ የንግድ መስመሮች መዘጋት፣ ተደጋጋሚ የውጭ ወራሪዎች ጥቃት፣ የዓባይ ወንዝ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች እና የቀዝቃዛው ጦርነት አሰላለፎች የሀገሪቱ አቅም በልማት ላይ እንዳይውል ወደኋላ የጎተቱ ውጫዊ ፈተናዎች ነበሩ።
ከቀደመው የአክሱም ሥልጣኔ ዘመን ጀምሮ እስከ 1980ዎቹ ድረስ ትቆጣጠረው ከነበረው ቀይ ባሕር እንድትገለል በማድረግ የልማት እና የቴክኖሎጂ ሽግግር ጉዞዋን ለረጅም ዘመናት አቀዛቅዘውታል። በወራራዎች የተደረጉ የወረራ ሙከራዎች እና ከዚያ በኋላ የተከፈቱ ተደጋጋሚ ጥቃቶችም ኢትዮጵያ ለልማት ሳይኾን ለሉዓላዊነቷ ትኩረት እንድትሰጥ፣ ያላትን አቅምም በሙሉ ወደ ሉዓላዊነት ማስከበር እንድታዞር አስገድደዋታል።
በተጨማሪም በዓባይ ወንዝ አጠቃቀም ዙሪያ የተሰነዘሩ ዲፕሎማሲያዊ ጫናዎች የልማቷ ትልቅ ማነቆ ኾነው ቆይተዋል። በሌላ በኩል የዓለም ልዕለ-ኀያላን ሀገራት የነበራቸው ጣልቃ ገብነት እና የርዕዮተ-ዓለም ጫና ሀገሪቱ የተረጋጋ የኢኮኖሚ ፖሊሲ እንዳይኖራት በማድረግ የልማቷን ቀጣይነት ያናጉ እና ሀገሪቱን የጂኦ-ፖለቲካዊ ፍላጎቶች መፈተኛ አውድማ ያደረጉ ነበሩ።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በመደመር መንግሥት ምሥረታ ላይ ባደረጉት ንግግር የታላላቅ ኀያላን መራኮቻ በኾነው በመካከለኛው ምሥራቅ እና በባብ ኤል መንደብ ቀጣና መገኘታችን ፈተናም ዕድልም እንዳለው አንስተዋል።
የኀያላኑ ሽኩቻ በተደጋጋሚ የኢትዮጵያን ቅርጽ እንደወሰነውም አንስተዋል። ኢትዮጵያም ነጻነቷን ለማስከበር ስትል ትኩረቷ ከልማት ወደ ጦርነት እንዲዞር ማድረጉን ጠቅሰዋል።
የባሕር በር ተጋሪነታችን የተለወጠው እና የተጽዕኖ አድማሳችን ሲኮሰምን የኖረውም ተገደን እንደኾነ ገልጸዋል። ባልተዘጋጀንበት ወቅት ደግሞ መውጫ መግቢያ በራችን ተዘግቶብናል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት ዓመታት በመጣንበት መንገድ ብዙ ፈተናዎችን አልፈናል በማለት በቀደሙት ዘመናት የነበሩት የውጭ ጫናዎች አሁንም መቀጠላቸውን ጠቅሰዋል። የኢትዮጵያ ለውጥ ያስደነገጣቸው አካላት በክፉ ዐይናቸው ማየት እንደጀመሩ፤ ባዳ እና ባንዳዎች ልማት እና ዕድገቷን ለማደናቀፍ ብዙ እንደሞከሩ ጠቁመዋል። ኢትዮጵያን ግን አልቻሏትም፤ አይችሏትም ብለዋል።
ኢትዮጵያ ትንግርት ናት ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ “ውድቀቷን ሲመኙ ትነሳለች፤ ድክመቷን ሲናፍቁ ጠንክራ ትወጣለች፤ ተበተነች፣ አለቀላት ብለው ሳይጨርሱ ተሠብሥባ ትገኛለች ብለዋል።
ኢትዮጵያ በቀጣናችን ዋና ሀገር መኾኗን ብቻ ሳይኾን በቀጣናው ጉዳይ ላይ የምትወስን መኾኗን በሰዎች ችሮታ ሳይኾን በሥራዋ ታረጋግጣለች ነው ያሉት።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
