📌 ከካይሮ እስከ አስመራ የተዘረጉ የጥፋት መንገዶችን ያከሸፈችው ኢትዮጵያ

12

 

ከካይሮ እስከ አስመራ የተዘረጋው ኢትዮጵያ ካደገች ስጋት ናት በሚል የሚጎነጎን የጥፋት ተንኮል ዛሬም አልከሰመም፤ ኢትዮጵያም ሁሌም ንቁ እንድትኾን አስችሏታል።

የኢትዮጵያን የሉዓላዊነት አውድ ማናጋት፣ የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ግንባታን እና የውኃ አጠቃቀምን ማስተጓጎል፣ ሀገሪቱ በምሥራቅ አፍሪካ ያላትን ማዕከላዊ ሚና ማስቀረት ቀዳሚ ዓላማ በማድረግ ይሠራሉ።

ግብጽ የኢትዮጵያን የውስጥ ሰላም እንደ ብቸኛ የጂኦፖለቲካ ጫና መሣሪያ በመጠቀም የውስጥ ታጣቂዎችን በገንዘብ፣ በሥልጠና እና በሎጅስቲክስ በመደገፍ ኢትዮጵያን የማተራመስ ርካሽ ዘመቻ ስትመራ ቆይታለች።

እስራኤላዊው የታሪክ ተመራማሪ ፕሮፌሰር ሐጋይ ኤርሊክ ግብጽ በታሪኳ ኢትዮጵያን በወታደራዊ ኀይል ለመቆጣጠር ያደረገችው ሙከራ በጉንደት እና በጉራዕ ጦርነቶች ሙሉ በሙሉ መክሸፉን ያስታውሳሉ። ግብጽ በቀጥታ ማሸነፍ ሲሳናት የውስጥ ክፍተቶችን እና ተላላኪ ኀይሎችን በመጠቀም ኢትዮጵያን የማዳከም የረጅም ጊዜ ስትራቴጂ እንድትከተል አስገድዷታል ይላሉ።

ሻዕቢያም የዚህ ሴራ ዋና አስፈጻሚ በመኾን ለፀረ-ኢትዮጵያ ኀይሎች መጠለያ፣ የሥልጠና ማዕከል እና የጦር መሳሪያ ማስተላለፊያ ኮሪደር በመኾን እያገለገለች ነው። ከዚህም በላይ ቀጣናውን አለመረጋጋት ውስጥ በመክተት ኢትዮጵያ በኢኮኖሚ እንዳትለመልም እና የፖለቲካ መረጋጋት እንዳይኖራት የማድረግ የተቀናጀ የጥፋት አጀንዳ ተነድፎባታል።

በኢትዮጵያ ላይ የተከፈተው የውጭ ኀይሎች ሴራ እና የውስጥ ተላላኪዎች ትብብር ግን በኢትዮጵያ መንግሥት እና ሕዝብ ጽናት ሲመክን ኖሯል። አሁንም ተስፋ በሚያስቆርጣቸው ልክ አላማቸው እየከሸፈ የኢትዮጵያ ታሪካዊ አሸናፊነት ሕያው ኾኗል።

ሀገሪቱ ሕልውናዋን አስጠብቃ ማቆየት የቻለችው በሕዝቧ ጥልቅ የሀገር ፍቅር ስሜት እና በጸጥታ መዋቅሯ ደኅንነትን የማስከበር አቅም ነው። የካይሮ እና የአስመራ ሴራዎች በተደጋጋሚ የከሸፉት ኢትዮጵያ ባላት ሰፊ የጂኦፖለቲካዊ ቁመና፣ በሕዝቧ ብዝኀነት ውስጥ ባለው የጋራ መግባባት እና የሉዓላዊነት ስሜት ነው።

የሕዳሴው ግድብ መጠናቀቅ ራሱ የዚህ የማክሸፍ ብቃት ትልቁ ማሳያ ነው። የውጭ ኀይሎች የፈጠሯቸውን መሰናክሎች በሕዝብ አቅም ብቻ በመስበር ወደ ፍጻሜ ማድረስ መቻሉ የኢትዮጵያን ጽናት ያረጋገጠ ክስተት ነው።

ይሁን እንጂ የጥፋት መንገዶቹ ሙሉ በሙሉ አልተዘጉም፤ አሁንም አደጋው ቀጥሏል። ይህንም የተረዳው ሕዝብ የጥፋት ኃይሎችን እያወገዘ ነው። የአማራ ክልል ሕዝብ የውስጥ እና የውጭ ሴራዎችን እና ሉዓላዊነቱን አደጋ ላይ የጣለውን አሻጥር በመቃወም በአደባባይ መውጣቱ የነቃ ሕዝባዊ ንቃተ-ህሊና ማሳያ ነው።

ኢትዮጵያ የውጭ ሴራዎችን ዛሬም እንደ ትናንቱ ማክሸፍ የምትችለው ሕዝቧን አስተባብራ፣ የሕግ የበላይነትን አረጋግጣ እና ውስጣዊ ሰላሟን በመገንባት ነው።

#የመደመር_መንግሥት!

#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹

#አሚኮ ​#Ethiopia_Geo_politics #Sovereignty #Resilience

#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_28_2019_ዓ_ም

✍️:- በስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleኢትዮጵያ እና አሜሪካ ታሪካዊ ግንኙነታቸውን እና ቀጣናዊ ስትራቴጂክ አጋርነታቸውን ለማጠናከር ተስማሙ።
Next articleለጥንቃቄ፦ ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ይኖራል!