
የሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የአስፈጻሚ አካላትን ስያሜ፣ አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን የቀረበውን ረቂቅ አዋጅን በትናንትናው ዕለት በሙሉ ድምፅ ማፅደቁ ይታወሳል።
ረቂቅ አዋጁም አዋጅ ቁጥር 1440/2019 ዓ.ም ሆኖ ጸድቋል። የማሻሻያው ዋና ዓላማ ተቋማት ሥራቸውን በግልጽ እንዲያውቁ፣ የጋራ እና የተናጠል ኃላፊነቶች እንዲለዩ እና የመንግሥት አፈጻጸም የበለጠ ቀልጣፋ እንዲሆን ነው።
ይህም በተቋማት መካከል የሚፈጠርን የሥራ መደራረብ በመቀነስ፣ ኃላፊነትን በመለየት እና ተጠያቂነትን በማጠናከር የመንግሥትን የማስፈጸም አቅም ያሳድጋል። የዚህ ለውጥ ዋና ተጠቃሚው ደግሞ ዜጎች ናቸው።
የተደራጀ ተቋም ማለት የተሻለ አገልግሎት፣ የተገለጸ ኀላፊነት ማለት የበለጠ ተጠያቂነት፣ በተሻለ ኹኔታ የሚመራ የሕዝብ ሀብት ማለት ደግሞ የበለጠ ውጤት ማለት ነው።
ማሻሻያው ባለፉት አምስት ዓመታት በአስፈጻሚ ተቋማት የታዩ ውስንነቶችን ለመቅረፍ ጠንካራ መሠረት እንደሚፈጥር ተገልጿል።
በአዋጁ መሠረት ከቁጥር አንፃር ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች በነበሩበት 22 ኾነው መቀጠላቸው እና በሁለት ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቶች ላይ የስያሜ ለውጥ ሲደረግ፣ ሁለት ሚኒስቴሮች አንደ አዲስ ተቋቁመዋል።
