“የቀይ ባሕር ባለቤቶች፤ የባሕር በር ባለ እርስቶች”

13

 

ገዢውን ባሕረ ነጋሽ፤ ግዛቱን መረብ ምላሽ እያለች ዘመናትን ኖራለች። ገና ከጥንት ዘመን ጀምሮ በባሕሯ

ከሥልጣኔ ላይ ሥልጣኔ ደራርባለች፤ በባሕሯ ከዓለም ቁንጮ የንግድ መዳረሻዎች ቀዳሚዋ ኾናለች፤ በባሕሯ አያሌ መርከቦችን ጭናለች፤ በባሕሯ ወታደሮቿን አሥፍራ ሉዓላዊነቷን ጠብቃለች።

ለሙሴ በበትር የተከፈለለት፤ እስራኤላውያን ከባርነት ወደ ምድረ እርስት የተሻገሩበት፤ ፈርኦን ከእነ ሠራዊቱ የጠፋበት፤ ንግሥተ ሳባ በታላቅ አጀብ ያለፈችበት፤

ኀያላን ነገሥታት ኀያል ታሪክ የሠሩበት፤ ሥልጣኔ እንደ ጀንበር የደመቀበት፤ ገናና ታሪክ የሚነገርለት ያ ባሕር የጥንታዊቷ ሀገር የኢትዮጵያ ነው። ይህም ባሕር ቀይ ባሕር ይሰኛል።

በዚህ ባሕር ሃይማኖተኞች፤ ነጋዴዎች፣ ሀገር አሳሾች፤ ፖለቲከኞች፤ የጦር አበጋዞች ተመላልሰውበታል።

ኢትዮጵያውያን ነገሥታት በቀይ ባሕር አያሌ ታሪኮችን ሠርተውበታል። የውጭ ግንኙነታቸውን በዚሁ ባሕር ላይ አጽንተዋል። የሚመጣውን በወደባቸው ተቀብለዋል። የሚሄደውንም በወደባቸው ሸኝተዋል።

በቀይ ባሕር ላይ የኢትዮጵያ መርከቦች ለዘመናት ተመላልሰዋል። የበዙት ወደቦቿ በመርከቦቿ ተጨናንቀዋል። ነገሥታቱ የባሕር ኀይላቸውን

አጠንክረው የሀገራቸውን ሉዓላዊነት ጠብቀዋል። የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል አባላት ለዘመናት በጽናት ቆመዋል። ኢትዮጵያውያን ነጋዴዎች በቀይ ባሕር
ንግዳቸውን አጧጡፈዋል።

ለኢትዮጵያ የሥልጣኔ መድመቅ የባሕሯ የቀይ ባሕር አስተዋጽኦ የላቀ ነበር። ለዚያም ነው አያሌ ኢትዮጵያውያን መረብ ምላሽ እየሄዱ ለሀገራቸው ሉዓላዊነት መስዋዕትነት ሲከፍሉ የኖሩት።

የናፓታ እና የመርዌ ሥልጣኔዎች የገነኑት፤ የአክሱም ሥልጣኔ በዘመኑ አቻ ያልተገኘለት፤ ከዚያም ቀጥለው

የመጡ ሥልጣኔዎች በዓለም መድረክ የደመቁት ዝም ብለው አልነበረም። ባሕሯን ተንተርሰው በደመቁ ንግዶቿ፤ በሌሎች ዓለማት በማይገኙ ማዕድኖቿ ነበር እንጂ።

አምባሳደር ዘውዴ ረታ የኤርትራ ጉዳይ በተሰኘው መጽሐፋቸው ጣልያን ኤርትራ ብሎ ስም ከማውጣቱ አስቀድሞ ይህ ክፍለ ሀገር ” መረብ ምላሽ፤ ምድረ

ሐማሴን” እየተባለ ይጠራ እንደነበር ጽፈዋል። ክፍለ ሀገሩ መረብ ምላሽ፣ የክፍለ ሀገሩ ገዢም ባሕረ ነጋሽ እየተባለ ይጠራ እንደነበርም ይነገራል። ይህ ምድር

የኢትዮጵያ ሰሜናዊ ክፍለ ሀገር ኾኖ ዘመናትን ተሻግሯል። ከኢትዮጵያ ታሪክም ነጥሎ ማየት አይቻልም።

ከክርስቶስ ልደት በፊት በመጀመሪያው እና በሁለተኛው ሺህ ዓመታት ጀምሮ ኢትዮጵያ ከውጭ የሚመጡትን እንግዶቿን ስትቀበል የነበረችው በዚሁ በክፋዩዋ ምድር በኩል እንደኾነ አምባሳደር ዘውዴ መዝግበል።

ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ሲያንስ እስከ ቀይ ባሕር ያለውን እና ቀይ ባሕርን ጨምሮ፣ ከፍ ሲል ደግሞ ከቀይ ባሕር ማዶ ያለውን ምድርም ይገዙ እና ያሥተዳድሩ ነበር።

የጥንታዊው የኢትዮጵያ መናገሻ ከተማ አክሱም እና በአካባቢው የሚገኙ የታሪክ ቅርሶች እና ሐውልቶች የኢትዮጵያን ጥንታዊ ሥልጣኔ ያስረዳሉ። ስለዚህም

መረብ ምላሽ ወይም ምድረ ሐማሴን በተባለው የኢትዮጵያ ክፍል የሚኖሩ ወገኖች ለኢትዮጵያዊነታቸው የተለየ ማስረጃ ማቅረብ አያስፈልግም ብለው ጽፈዋል።

የኢትዮጵያ ነገሥታት መንበር ከአክሱም ወደ ሮሃ ላስታ፣ ከላስታ ወደ ሸዋ፣ ከሸዋ ወደ ጎንደር እያለ በተዘዋወረበት ዘመንም የኢትዮጵያ ነገሥታት “ባሕረ

ነጋሽ” እየተባሉ በንጉሠ ነገሥቱ በሚሾሙ ታላላቅ ሰዎች ሲተዳደር የኖረ ነው። የቀይ ባሕር ፈተናዎች ቢበዙበትም የኢትዮጵያ ነገሥታት ባሕራቸውን ከመጠቀም አልተመለሱም ነበር።

በሪሁን ከበደ የአጼ ኃይለ ሥላሴ ታሪክ በተሰኘው መጽሐፋቸው ቀይ ባሕር ባሕራችን፣ የአዶሊስ፣ የምጽዋ ወደባችን፤ በባሕራችን ውስጥ የሚገኙት ዳሕላቅ

እየተባሉ የሚጠሩት 350 ደሴቶቻችን፤ በባሕሩ ውስጥ ተመልተው የሚገኙት የጨውና እና የዓሣ ሀብታችን ጠላቶች የሚበዙባቸው ናቸው ብለው ጽፈዋል።

ጣልያን ኤርትራ ብላ ከመሰየሟ አስቀድሞ ባሕሩን እና የብሱን፣ ወደቡን እና ደሴቱን በአንድ ላይ አጠቃልሎ የሚያሥተዳድር ባሕረ ነጋሽ እየተባለ ከጥንት ጀምሮ

በኢትዮጵያ መንግሥት የሚሾም ለመኾኑ የታወቀ ነው ይላሉ። የባሕሩ፣ የምድሩ እና የወደቡ የእርሱ ባለቤት የኢትዮጵያ ነውም ብለው ጽፈዋል። መረብ ምላሽ ( ኤርትራ) ጥንትም የኢትዮጵያ አካል ናት።

ለዘመናት ከኢትዮጵያ ጋር የኖረች ናት። ኢትዮጵያ በታሪክ ከታወቀችበት ዘመን ጀምሮ መረብ ምላሽ (ኤርትራ) የኢትዮጵያ አንደኛዋ ክፍል እና አካል ኾና የኖረች

መኾኗን ማስረጃ የማያሻው የተረጋገጠ በታሪክ የተመሰከረ ነው። የኢትዮጵያ የሥልጣኔ ምንጮች ከኾኑት ክፍለ ሀገራት አንደኛዋ ናት ብለው ጽፈዋል።

ቀይ ባሕር እና መረብ ምላሽ ጠላቶች የሚበዙበት ነውና ኢትዮጵያውያን ነገሥታት ሀገሩን ለማደላደል እና ወሰኑን ለማስጠበቅ መስዋዕትነት ሲከፍሉ ኖረዋል።

ይህን ሥፍራ አደላድለው ከገዙት ነገሥታት መካከል ደግሞ ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ አንደኛው ናቸው።

ግርማዊ ቀዳማዊ አጼ ኃይለ ሥላሴ በመስከረም 24/1945 ዓ.ም መረብ ምላሽን ሊጎበኙ በሄዱበት ጊዜ እንዲህ ብለው ነበር። ” ግዛታችን ኤርትራን፣

የባሕር ጠረፋችንን ለመጎብኘት ስንሄድ በመካከል ለያይቶ የነበረው ሰው ሠራሽ ድንበር ተደምስሶ የድንበሩን በር ከፍተን የመረብን ወንዝ በዚህ ሥፍራ ለመሻገራችን መታሰቢያ ለትውልድ ይቆይለት።

ይህ አካባቢ ኤርትራ እየተባለ የተጠራው ከዛሬ 60 ዓመት በኋላ ጀምሮ ነበር። ከዚያ አስቀድሞ ግን ይህ ግዛት ከንጉሠ ነገሥት መንግሥት ግዛታችን ስም

ከኢትዮጵያ የተለየ መጠሪያ የለውም ነበር። ለዚህ ዘመናት ሙሉ የኤርትራ ግዛት የኢትዮጵያ የባሕር መዳረሻ ናት። በአባቶቻችን ነገሥታት ምድረ ሐማሴን ይባል የነበረ ነው” ብለው ነበር።

ይህ ምድረ ሐማሴን እና ቀይ ባሕር ከ30 ዓመታት በፊት በስህተት ከመሄዱ አስቀድሞ የኢትዮጵያ መውጫ እና መግቢያ የኾነ የቀደመ እርስቷ ነበር። የኢትዮጵያ የባሕር

ኀይል መሠረትም በዚሁ በቀይ ባሕር ነው። ለዚህም ነው ኢትጵያውያን የቀይ ባሕር ባለቤቶች፤ የመረብ ምላሽ ባለ እርስቶች የሚባሉት።

በሪሁን ሲጽፉ የኢትዮጵያን ክፋይ ባሕረ ነጋሽን ወይም ኤርትራን ፈርሞ አሳልፎ መስጠት እና ማስረከብ የአሁኑንም ኾነ የተከታዩን ትውልድ በጣም የሚያሳዝን፤

ይቅርታ የማይገኝለት ትልቅ የጥፋት ታሪክ ነው ብለዋል።
አሁን ከዓመታት በኋላ ኢትዮጵያ እና ኢትዮጵያውያን በቀደመው ባሕራችን እንጠቀም ብለው ጠይቀዋል።

ስለምን ቢሉ ቀይ ባሕር ባሕራቸው ነውና። ለዘመናት ሥልጣኔን ያረቀቁበት ነውና። በዚህ ዘመን ያስፈልጋቸዋልና። የታሪካቸው አንድ አካል ነውና። ወደ ባሕራቸው መመለሳቸው፣ ባሕራቸውንም ማሥተዳደራቸው የሚቀር አይመስልም።

#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_28_2019_ዓ_ም

✍️ በታርቆ ክንዴ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article🌾 ዘመናዊ ግብርና ለምግብ ሉዓላዊነት
Next articleበሐረሪ ክልል 5 ሺህ ሔክታር መሬት የሚሸፍን የበጋ መስኖ ልማት ተጀመረ።