
“ራት እና መብራት አይንሳችሁ!” ይላሉ ኢትዮጵያውያን በቀደመው ብሂላቸው። የትልቋ ሀገር ኢትዮጵያ ሕዝቦች ታላቅ ርዕይ ሰንቀው እና በተባበረ ክንድ ሠርተው ከኢትዮጵያም አልፎ ለሌሎች አፍሪካውያን ጎረቤት ሀገራት የሚተርፍ የራት እና መብራት በረከትን የያዘ ስም ተክለዋል – ታላቁ የሕዳሴ ግድብ።
ኢትዮጵያ የዓባይን ውኃ ለልማቷ በፍትሐዊነት እና በምክንያታዊነት የመጠቀም መብቷን በተግባር ያረጋገጠችበት ታሪካዊ ክስተት ነው።
ታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ የኤሌክትሪክ ብርሃን በመስጠት ብቻ ሳይወሰን ለኢትዮጵያ ሕዝቦች እና ለጎረቤቶች ራትንም መብራትንም የሚያጋራ የጋራ የዕድገት ምልክት ኾኗል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ስለ ሕዳሴ ግድብ ሀገራዊ እና ቀጣናዊ ፋይዳ በሰጡት ማብራሪያ ግድቡ ለኢትዮጵያ የነበረውን የኀይል እጥረት ከመቅረፉ ባለፈ ለቀጣናው ኢኮኖሚያዊ ትስስር መሠረት መጣሉን አጉልተው አሳይተዋል።
የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የፈጠረው ሰፊው የንጋት ሐይቅ ከፍተኛ የዓሳ ምርት በመስጠት ኢኮኖሚውን እየደገፈ ይገኛል። በአሁኑ ወቅት በአካባቢው የሚመረተው ዓሳ የሀገር ውስጥ ፍላጎትን ከመሸፈን አልፎ ለውጭ ገበያ እየቀረበ ነው።
ለአካባቢው ማኅበረሰብም ሰፊ የሥራ ዕድል እና የኢኮኖሚ መነቃቃት ፈጥሯል።
የታላቁ የሕዳሴ ግድብ ትላንት በጨለማ ይኖሩ ለነበሩ ሚሊዮን ኢትዮጵያውያን የመብራት አገልግሎት ከመስጠት ባሻገር ለሀገር ውስጥ አምራች ኢንዱስትሪዎች እና ለኢንቨስትመንት ዘርፉ አስተማማኝ የኤሌክትሪክ ኀይል አቅርቦት በመስጠት አዲስ ሕይወት ዘርቷል።
ኢትዮጵያ ያላትን ተፈጥሮአዊ ሃብት ለብቻዋ ከመጠቀም ይልቅ ከጎረቤቶቿ ጋር በጋራ የመልማት መርሕን አጥብቃ እንደምትከተል ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በተደጋጋሚ መግለጻቸው ይታወሳል።
“የታላቁ ሕዳሴ ግድብ የኢትዮጵያውያን የጽናት ውጤት ብቻ ሳይኾን የምሥራቅ አፍሪካ ሀገራት በጋራ የሚያድጉበት እና የሚበለጽጉበት የጋራ ሃብታችን ነው!” ብለዋል።
ሀገሪቱ ከሕዳሴው ግድብ የሚመነጨውን ንጹህ የኀይል ምንጭ ለሱዳን፣ ጂቡቲ፣ ኬንያ እና ደቡብ ሱዳን እያቀረበች ነው። የቀጣናውን ኢኮኖሚያዊ ትስስር ከማጠናከሩ ባሻገር ከምሥራቅ አፍሪካ ያለውን ጋራ ዲፕሎማሲዊ ግንኙነት በማጠናከር እና የልማት ጉዞን በማፋጠን አይተኬ ሚና እየተጫወተም ነው።
በምርቃት መርሐ ግብሩ የተገኙት የኬንያው ፕሬዝዳንት ዊልያም ሩቶ ታላቁ የሕዳሴ ግድብ “አፍሪካ የራሷን ሃብት ተጠቅማ ዕጣ ፈንታዋን መወሰን እንደምትችል እና ብቃት እንዳላት ማረጋገጫ ተምሳሌት ነው” ማለታቸው ይታወሳል።
#የሕዳሲ_ግድብ #ኢኮኖሚያዊ_ተጠቃሚነት #ኢትዮጵያ #አሚኮ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
