የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ተስፋ ኾኖ ብቅ ያለው ፋብሪካ!

7

 

በኢትዮጵያ ሶማሌ ክልል ጎዴ ከተማ እየተገነባ የሚገኘው ግዙፍ የማዳበሪያ ፋብሪካ ሀገሪቱ ግብርናን ለማዘመን እና የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የወሰደችው ስትራቴጂካዊ እርምጃ አንዱ ማሳያ ነው።🏗️

ፋብሪካውን ለመገንባት ስምምነት በተካሄደበት ወቅት ማብራሪያ የሰጡት የገንዘብ ሚኒስትር አሕመድ ሽዴ ፕሮጀክቱ በ2 ነጥብ 5 ቢሊዮን ዶላር የሚገነባ ነው። ፋብሪካው የዩሪያ ማዳበሪያን በማምረት ለገበያ የሚያቀርብም ይኾናል። የተፈጥሮ ጋዝ በማልማትም የማዕድን ዘርፍ ልማቱን እንደሚደግፍም ተናግረዋል።

እንደ ሚኒስትሩ ማብራሪያ ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን የግብርና ዕድገት የሚያሳልጥ፣ የውጭ ምንዛሬ ጫናን የሚያቃልል እና የቀጣናው የኢኮኖሚ አንቀሳቃሽ ለመኾንም ያለመ ነው። ለበርካታ ዜጎች የሥራ ዕድል በመፍጠር እና ኢንዱስትሪውን በማነቃቃት ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት ሚናው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።📈

ኢትዮጵያ በየዓመቱ ለማዳበሪያ ግዥ የምታወጣውን በቢሊዮን ዶላር የሚቆጠር ወጭ በማዳን በሀገር ውስጥ ምርት ለመተካት የሚያስችልም ነው። የሀገሪቱን የግብርና ምርት እና ምርታማነት ለማሳደግ ​ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚያበረክትም አመላክተዋል።

ፋብሪካው ሲጠናቀቅ ​የኢትዮጵያ አርሶ አደሮች ለዘመናት ሲያነሷቸው የነበሩት ማዳበሪያ በወቅቱ አለመድረስ፣ ከመጠን ያለፈ የዋጋ ንረት እና የአቅርቦት እጥረት ጥያቄዎችን የሚፈታ ነው።

ማዳበሪያ በሀገር ውስጥ መመረቱ የትራንስፖርት ወጭን በመቀነስ አርሶ አደሮች በተመጣጣኝ ዋጋ እና በትክክለኛው የምርት ወቅት ግብዓቱን እንዲያገኙ ያስችላቸዋል። 🚛

ግዙፉ ኩባንያ ዳንጎቴ ግሩፕ ከኢትዮጵያ ኢንቨስትመንት ሆልዲንግ ጋር በመኾን የሚገነባው ይህ ግዙፍ ፕሮጀክት ኢትዮጵያ ለውጭ ኢንቨስትመንት ያላትን ምቹነትም የሚያሳይ ነው።

ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) እንደተናገሩት ፋብሪካውን በ40 ወራት ለማጠናቀቅ ውል ተወስዷል። ነገር ግን ከ40 ወራት ባነሰ ጊዜ ውስጥ በማጠናቀቅ በኢትዮጵያ አንዱ ቁልፍ የኾነውን የማዳበሪያ አቅርቦት ችግር ለመፍታት ጥረት እየተደረገ ነው ብለዋል። ለዚህም በመንግሥት በኩል አስፈላጊው ክትትል እና ድጋፍ እየተደረገለት መኾኑን አንስተዋል።

ፕሮጀክቱ የሀገሪቱን መልክ የሚቀይር እና የኢኮኖሚ አቅሟን የሚያሳድግ ኢንቨስትመንት መኾኑን አመላክተዋል። ፋብሪካው ወደ ሥራ ሲገባ ከሀገር ውስጥ ፍጆታ በተጨማሪ ለውጭ ገበያ ለማቅረብ ታሳቢ ተደርጎ እየተሠራ መኾኑንም ጠቁመዋል።

#አሚኮ #Investment #Ethiopia🇪🇹

‎#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም

✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
‎
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous articleራትም መብራትም! – ታላቋ ሀገር ኢትዮጵያ አልማ ያሳካችው ሀገራዊ እና ቀጣናዊ በረከት
Next articleወይዘሮ ጫልቱ ሳኒ የፌዴራል ቤቶች ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስፈጻሚ ኾነው ተሾሙ።