
የደቡብ ወሎ ዞን የ2018 ዓ.ም የክረምት የዜጎች በጎ ፍቃድ አገልግሎት ማጠቃለያ እና የ2019 ዓ.ም የበጋ የዜጎች በጎ ፍቃድ አገልግሎት የማስጀመሪያ መርሐግብር በደሴ ከተማ አካሂዷል። በመርሐ ግብሩ ላይ በዞኑ የሚገኙ የከተማ አሥተዳደር እና የወረዳ የሥራ ኀላፊዎች ተገኝተዋል።
አሚኮ ያነጋገራቸው የሐይቅ ከተማ አሥተዳደር እና የጃማ ወረዳ ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ ጽሕፈት ቤት ኀላፊዎች በክረምት በጎ ፍቃድ ማኀበረሰቡን ተጠቃሚ ያደረጉ የተለያዩ ሥራዎችን ማከናወናቸውን ገልጸዋል።
ከእነዚህም ውስጥ ለአረጋውያን የመኖሪያ ቤት ሥራ፣ የደም ልገሳ፣ የአረንጓዴ አሻራ፣ የአካባቢ ልማት እና በርካታ የበጎ ፈቃድ ሥራዎች መከናወናቸውን ነው ኀላፊዎቹ ያነሱት።
የደቡብ ወሎ ዞን ሴቶች፣ ወጣቶች እና ማኀበራዊ ጉዳይ መምሪያ ኀላፊ ቤተልሄም ብርሀኑ በ2018 ዓ.ም የክረምት በጎ ፍቃድ አገልግሎት መንግሥት ባስቀመጠው አቅጣጫ መሠረት እንደዞን በትኩረት መከናወኑን አንስተዋል።
በተለይም ዞኑ ባከናወነው ድንበር ተሻጋሪ የበጎ ፍቃድ አገልግሎት ሥራ በኦሮሚያ እና አፋር ክልሎች ለተቸገሩ ወገኖች አስፈላጊውን ድጋፍ የማድረግ ሥራ መሠራቱንም መምሪያ ኀላፊዋ ጠቁመዋል።
መንግሥት ሊያወጣ የሚችለውን ከ3 ቢሊዮን ብር በላይ ማዳን ተችሏል ያሉት ወይዘሪት ቤተልሄም ይህንን በጎ ሥራ ለመሥራት የተለያዩ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ያልኾኑ ተቋማትም ድርሻቸው የጎላ መኾኑን አንስተዋል።
በብልጽግና ፓርቲ የደቡብ ወሎ ዞን ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ተስፋ ዳኘው በክረምት በጎ ፍቃድ የታዩ መልካም ተሞክሮዎችን በበጋ መድገም እና ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ የሚያደርጉ ሥራዎች መሠራት እንዳለባቸው መልዕክት አስተላልፈዋል።
በመድረኩ በበጎ ፈቃድ አገልግሎት የተሻለ አፈፃፀም ለነበራቸው ዕውቅናም ተሰጥቷል።
በሰልሀዲን ሠይድ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
