
በደቡብ ወሎ ዞን የ2019 በጀት ዓመት የመስኖ ልማት እና የተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ የንቅናቄ መድረክ ተካሂዷል።
የወረኢሉ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ ጌታቸር ተስፋዬ በወረዳው በመስኖ የማምረት ልምድ እያደገ መምጣቱን ገልጸዋል። በበጋ መስኖ ስንዴ ሜካናይዜሽን እና ዘመናዊ የግብርና ግብዓቶችን በአግባቡ ስለሚጠቀሙ አርሶ አደሮች ወደ ትርፍ አምራችነት መሸጋገራቸውን ነው የተናገሩት።
የተሁለደሬ ወረዳ ግብርና ጽሕፈት ቤት ኀላፊ መሐመድ ጋሻው የተፈጥሮ ሀብት ሥራ በማኅበረሰቡ ዘንድ እንደ ባሕል እየኾነ መምጣቱን ገልጸዋል። በተሠሩ ተከታታይ የአካባቢ ጥበቃ ሥራዎች የወረዳው የደን ሽፋን ማደጉን ጠቁመዋል።
የሎጎ ሐይቅን ከደለል ለመከላከል በአካባቢው ያሉ ተራራማ አካባቢዎችን ከመከለል ጀምሮ በዙሪያው የተለያዩ አትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ሥራዎች እየተሠሩ መኾናቸውን ገልጸዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ግብርና መምሪያ ኀላፊ አሕመድ ጋሎ በዞኑ ባለፈው ዓመት ከ40 ሺህ ሄክታር በላይ መሬት በመስኖ መልማቱን አስታውሰዋል። በዚህ ዓመትም የውኃ አማራጮችን ሁሉ በመጠቀም በስንዴ እና በፍራፍሬ ልማት አመርቂ ውጤት ለማስመዝገብ በቅንጅት ሥራዎች እየተሠሩ ነው ብለዋል።
በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራዎችም በውኃ ሀብት እና በሥራ ዕድል ፈጠራ ተጨባጭ ውጤት መምጣቱን አስረድተዋል። በዚህ ዓመትም ተፋሰስን መሠረት ያደረጉ በ1 ሺህ 400 ተፋሰሶች ላይ የሥነ ሕይወታዊ ሥራዎች ይከናወናሉ ብለዋል።
የደቡብ ወሎ ዞን ዋና አሥተዳዳሪ አሊ መኮንን በምግብ ራስን የመቻል ንቅናቄን ለማሳካት መስኖ ልማት ላይ በሰፊው መሥራት ይጠበቃል ብለዋል። በተፈጥሮ ሀብት ጥበቃ ሥራ ላይም የሚታዩ ክፍተቶችን በማረም ከልማዳዊ አሠራር መውጣት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የመስኖ እና የፍራፍሬ ልማትን ለማሳካትም የችግኝ ጣቢያዎችን በራስ አቅም በዘመናዊ መልኩ ማደራጀት እንደሚገባ አንስተዋል።
ሥራዎቹ ሰፊ የሕዝብ ተሳትፎን የሚጠይቁ በመኾናቸው ማኅበረሰቡ በባለቤትነት እንዲሳተፍም አሳስበዋል።
ዘጋቢ፦ አንተነህ ፀጋዬ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
