የዓባይ ሸለቆን በረከት ወደ ምርት ለመቀየር ጫፍ የደረሰው የዓባይ ዳሩ ግዙፍ ፕሮጄክት!

7
የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጄክት በኢትዮጵያ ካሉት ግዙፍ ፋብሪካዎች መካከል አንዱ ኾኖ እየተገነባ ነው። ፕሮጄክቱ በአማራ ክልል ምሥራቅ ጎጃም ዞን ደጀን ወረዳ በዓባይ ሸለቆ የሚገኙ የማዕድን ሀብት ጸጋዎችን መሠረት አድርጎ የተቋቋመ ነው።
የዓባይ ሲሚንቶ ፋብሪካ ፕሮጄክት ሥራ አሥኪያጅ ኢንጂነር አስራት ኪዳኑ የፋብሪካው ግንባታ ቀደም ሲል በተለያዩ ምክንያቶች መጓተቶች ቢስተዋሉበትም በመንግሥት በኩል በተደረገው ልዩ ድጋፍ አሁን ላይ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ነው ብለዋል።
ፕሮጄክቱ በእስካሁኑ የሥራ አፈጻጸም ለጥሬ እቃነት የሚውሉ የማዕድን ማውጫ ሳይቶችን ማዘጋጀት፣ ከሳይቶች ወደ ፋብሪካው የሚያደርሱ ከ4 ነጥብ 5 እስከ 10 ኪሎ ሜትር የሚደርሱ የመንገድ መሠረተ ልማቶችን መዘርጋቱን አንስተዋል።
ከየትመን አካባቢ የውኃ ጉድጓዶችን በማስቆፈር 22 ኪሎ ሜትር በሚደርሱ በ4 መስመሮች ወደ ፋብሪካው ሳይት መሥመሮችን መዘርጋት፣ ለሳይት ተከላ መሬቱን የማዘጋጀት ሥራዎች መከናወናቸውን ጠቁመዋል። የ1 ነጥብ 8 ኪሎ ሜትር የውስጥ ለውስጥ መንገድ እና የ230 ኪሎ ቮልት የኤሌክትሪክ ኃይል እንዲሟላ መደረጉንም አስረድተዋል።
አጠቃላይ ፕሮጄክቱን በአጭር ጊዜ ለማጠናቀቅ አዲስ ውል ተፈርሞ ወደ ሥራ መገባቱን ነው የተናገሩት። አብዛኛው ማሽኖችም በውጭ ሀገር ተሠርተው ተጠናቅቀዋል ነው ያሉት። ወደ ሀገር ውስጥ መግባት እና መገጣጠም ብቻ እንደሚቀራቸውም ጠቁመዋል። የማዕድን ማውጫ ማሽኖች ተከላ በቅርቡ እንደሚከናወን ነው የተናገሩት።
አሁን ላይ ፕሮጄክቱ በከፍተኛ ፍጥነት እየተከናወነ ነው፤ አፈጻጸሙም 65 በመቶ ደርሷል ነው ያሉት። እስከ ነሐሴ 2019 ዓ.ም ለማጠናቀቅም እየተሠራ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
በፕሮጄክቱ ግንባታ ሂደት የልማቱ ተነሺዎችን ተጠቃሚ እያደረገ እንደሚገኝ አንስተዋል። ከ1 ሺህ 500 በላይ ለሚኾኑ ዜጎች የሥራ ዕድል ፈጥሯል። በቀጣይ ግንባታው ሲጠናቀቅ ከ3 ሺህ 500 እስከ 4 ሺህ ለሚደርሱ ዜጎች የሥራ ዕድል እንደሚፈጥር ተናግረዋል።
ፋብሪካው ወደ ማምረት ሲገባ በዓመት ከ2 ነጥብ 25 ሚሊዮን ቶን ሲሚንቶ እንደሚያመርት ገልጸዋል። ይህም በክልሉም ኾነ በሀገሪቱ የሚያጋጥመውን የሲሚንቶ እጥረት በመፍታት ለግንባታው ዘርፍ እድገት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እንደሚኖረው አብራርተዋል።
በተለይም ካለው የፋብሪካው ማዕከላዊነት አንጻር የክልሉን የሲሚንቶ ፍላጎት በማሟላት ለክልሉ ልማት በከፍተኛ ደረጃ እንደሚያግዝ አስታውቀዋል።
ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ኢትዮጵያ የአየር ላይ የበላይነትን መገንባት ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)
Next articleበምግብ ራስን ለመቻል የመስኖ ልማት ላይ በሰፊው መሥራት ይጠበቃል።