
ኢትዮጵያ የሀገሪቱን ሉዓላዊነት እና የአየር ክልል ደኅንነት ለማረጋገጥ ከሩስያ መንግሥት ጋር ባደረገችው ስምምነት መሠረት 12 የሱ-35 (Su-35 – 4++) ተዋጊ ጄቶችን ተረክባለች።
በርክክብ ሥነ ሥርዓቱ ላይ መልዕክት ያስተላለፉት
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአካባቢው ያሉ የጸጥታ ስጋቶች እና ዓለም አቀፍ አለመረጋጋቶችን በመገንዘብ ሀገራት በሰላም ጊዜ በቂ ዝግጅት ማድረግ አለባቸው ብለዋል።
በብዙ ጠላቶች የተከበበች እና 130 ሚሊዮን ሕዝብ ያላት ኢትዮጵያ ለሕልውናዋ የአየር ላይ የበላይነትን መገንባት ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ መኾኑን ተናግረዋል። በድሮን ብቻ ሳይኾን በSu-30 እና በSu-35 አቅምን መገንባት ያስፈልጋል ብለዋል።
ኢትዮጵያ አሁን የተረከበቻቸው የሱ-35 ጄቶች የአየር ለአየር እና የአየር ለምድር ውጊያዎችን ማካሄድ የሚያስችሉ እጅግ ዘመናዊ ቴክኖሎጂዎች የታጠቁ ናቸው።
የሱ-35 ጄቶች እስከ 200 ኪሎ ሜትር ርቀት ድረስ ክሩዝ እና ባሊስቲክ ሚሳይሎችን የመለየት እና የመከላከል አቅም አላቸው። ይህ ዕድገት ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች በሚገቡ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ በመኾን ከፍተኛ የመከላከያ ቴክኖሎጂን ማሥተዳደር የቻለች ሀገር መኾኗን ያሳያል።
ጦርነትን ማስቀረት የሚቻለው ጠንካራ የመከላከል አቅም ሲገነባ ብቻ መኾኑን ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል። “በልመና ወይም በችሮታ የምንጎናጸፈው ሉዓላዊነት አይኖርም” ያሉት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በቀጣይም በብቃት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ሀገር ለመገንባት ጥረቶች ይቀጥላሉ ነው ያሉት።
ኢትዮጵያ የኤስ-400 ሲስተም እና የሱ-35 ጄቶችን ሙሉ በሙሉ በሥራ ላይ ስታውል ከየትኛውም አቅጣጫ የሚመጡ የክሩዝ እና የባሊስቲክ ሚሳይል ጥቃቶችን በአየር ላይ የመጥለፍ እና የማክሸፍ አቅሟ እጅግ ከፍተኛ ደረጃ ላይ ይደርሳል።
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
