የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቃ።

7
የጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ ( ዶ.ር) የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቅቷል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በማኅበራዊ ትስስር ገጻቸው ባሰፈሩት መልዕክት ዛሬ የመደመር መጽሐፍ ወደ ሩሲያኛ ቋንቋ ተተርጉሞ ለንባብ በቅቷል። በተዘጋጀው የመጽሐፉ የምረቃ መርሐ ግብር ላይ በአካል ተገኝቼ በመካፈሌም ታላቅ ደስታና ኩራት ተሰምቶኛል ብለዋል።
ይህ ታሪካዊ ስኬት የመደመር ፍልስፍና ከኢትዮጵያ ሀገር በቀል ዕውቀት ተነስቶ ዛሬ ላይ ድንበር በመሻገር ወደ መላው ዓለም እየሰፋ መሄዱን የሚያሳይ ሕያው ማረጋገጫ ነው። ከዚህ በፊት መጽሐፉ ከሀገር ውስጥ ቋንቋዎች በተጨማሪ በእንግሊዝኛ፣ በቻይንኛ እና በአረብኛ ቋንቋዎች ተተርጉሞ ለብዙኃን አንባቢያን መድረሱን አስታውሰዋል። አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ ድንበር ተሻግሮ በሰፊው የሩሲያኛ ተናጋሪ ደጃፍ መድረሱ የፍልስፍናውን ዓለም አቀፋዊ ተደራሽነት እና ዲፕሎማሲያዊ ፋይዳ ይበልጥ ያጎለብተዋል ነው ያሉት።
ይህ እርምጃ የመደመርን ፍልስፍና፣ እሴቶች እና ሀሳቦች ከኢትዮጵያ አልፈው ለሌሎች ሕዝቦች የሚደርሱበትን አዲስ ዕድል ከመፍጠሩም በላይ፣ ኢትዮጵያ ለዓለም የምታበረክተው የራሷ የበሰለ ሀሳብ እንዳላት በተግባር የሚያሳይ ነው። ሩሲያ ለብዙ ኢትዮጵያውያን የሥነ ጽሑፍና የዕውቀት መማሪያ ምድር ኾና እንዳገለገለች ሁሉ፣ አሁን ደግሞ የኢትዮጵያ ሀሳብ በሩሲያኛ ቋንቋ ለሩሲያ አንባቢያን መድረሱ የዕውቀት ልውውጡን ሙሉ ያደርገዋል ብለዋል።
ለዚህ ስኬት መሳካት እና ለመጽሐፉ ዝግጅት ከፍተኛ አስተዋጽኦ ያበረከቱትን የሩሲያ ቱዴይ (RT) የመገናኛ ብዙኃን ባለሙያዎች እና መሪዎች ያደረጉትን ጥረትና ትጋት በከፍተኛ ደረጃ አደንቃለሁ።
ይህ አዲስ ታሪካዊ ምዕራፍ የኢትዮጵያን የበለጸጉ ሀገር በቀል ዕውቀቶች፣ ባሕሎች እና ፍልስፍናዎች በዓለም አቀፍ መድረክ ላይ ይበልጥ ለማስተዋወቅ እና በሕዝቦች መካከል ጠንካራ የባሕል እና የሃሳብ ድልድይ ለመገንባት የሚኖረው ሚና እጅግ ከፍተኛ ነው ብለዋል በመልዕክታቸው።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ባሕር ዳር ታላቅ ታሪክ እና ቅርስ የያዘች ውብ ከተማ ናት” የጣና ፎረም ተሳታፊዎች
Next article“ኢትዮጵያ የአየር ላይ የበላይነትን መገንባት ቅድሚያ የምትሰጠው ጉዳይ ነው” ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር)