
በተፈጥሮ የታደለች እና የሰው ዘር መገኛ የኾነችው ኢትዮጵያ የማይለወጥ የተፈጥሮ ጸጋዋ ከጥንት እስከ ዛሬ ዓለምን እያስደነቀ ይገኛል።
በባሕር ዳር ከተማ በተካሄደው በ12ኛው የጣና ፎረም የተገኙ ተሳታፊዎች በባሕር ዳር ከተማ የተፈጥሮ ገጸ በረከት እና በሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት ተደንቀው ምስክርነታቸውን ሰጥተዋል።
ኬኒያዊቷ የአፍሪካ ኅብረት የሰላም አምባሳደር ክሪስቲን ኦዲራ ባሕር ዳር ሲመጡ የመጀመሪያቸው መኾኑን ተናግረዋል። ከአዲስ አበባ ውጪ ያለውን የኢትዮጵያን ክፍል በማየታቸው ደስተኛ መኾናቸውን ገልጸዋል።
ሕዝቦቿ ውብ፣ እንግዳ ተቀባይነታቸው ግሩም፣ ምግቡም ጥሩ ኾኖ አግኝቸዋለሁ የሚሉት አምባሳደሯ በባሕር ዳር ከተማ ከጣና ሐይቅ የሚመጣው ነፋሻማ አየር የሚመች መኾኑን ተናግረዋል።
ሌላኛዋ የሰላም አምባሳደር እና የፎረሙ ተሳታፊ ሰንቲያ ቺጓኛ ባሕር ዳር የዓባይ ወንዝ መነሻ፣ ለኢትዮጵያ ብቻ ሳይኾን ለአፍሪካ እጅግ ታላቅ ታሪክን የያዘች ከተማ በመኾኗ የአሕጉራዊ ጉባኤ ማዕከል ለመኾን ተስማሚ ናት ብለዋል።
የሰላም አምባሳደሯ በከተማዋ አሕጉራዊ መድረኮችን የሚመጥኑ የጉባኤ ማዕከላት ተገንብተው መመልከታቸውን አንስተዋል። ይህም ባለፉት ዓመታት የታየውን እጅግ ከፍተኛ የመሠረተ ልማት ዕድገት የሚያሳይ ነው ብለዋል።
ከተማዋን ለማዘመን እየተከናወነ የሚገኘው ሥራ ከተማዋን ለዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ድንቅ የቱሪዝም መዳረሻ መኾን እንደሚያስችላትም አብራርተዋል።
ናይጄሪያዊው የፎረሙ ተሳታፊ ኢኬ ቹኩዌዜ ከተማዋ እንዲህ ዓይነት ትላልቅ መድረኮችን ማስተናገዷ ትልቅ ዕድል እና እውቅና የሚሰጣት ነው ብለዋል።
ከተማዋ ሰላማዊ በመኾኗ የኮንፈረንስ ቱሪዝም ማዕከል ለመኾን የሚያስችል ምርጥ እድል አላት ብለዋል። የከተማዋን ሰላም ጠብቆ በማስቀጠል፣ የሕዝቡ እንግዳ ተቀባይነት እና ሰው ወዳድነት ተጨምሮበት በቱሪስት ፍሰት ላይ ለውጥ ማምጣት እንደሚቻል አስገንዝበዋል።
በአዲስ አበባ ያዩትን ዓይነት የልማት እንቅስቃሴ በባሕር ዳርም ማየታቸውን፣ የመንገዶች ንጽሕና እና ጥራት፣ የመንገድ መብራቶቿ ውበት፣ እንደ አንድ አፍሪካ ሀገር የኤሌክትሪክ ኃይል አቅርቦት የማይቆራረጥባት መኾኑ እንዳስገረማቸው ገልጸዋል።
እንግዶቹ ከተማዋ አሁን ካለው በላይ ብዙ መልማት የሚችል ጸጋ ባለቤት መኾኗን ጠቁመዋል። በቀጣይ በሚኖሩ አሕጉራዊ መድረኮች ወደ ባሕር ዳር መመለስን በጉጉት እንደሚጠብቁም አመላክተዋል።
ዘጋቢ፦ አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
