
የምዕራብ ጎጃም ዞን ግብርና መምሪያ የ2019 በጀት ዓመት የበጋ መስኖ ልማት የንቅናቄ መድረክ አካሂዷል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ዕድሜዓለም አንተነህ የምግብ ሉዓላዊነትን ለማስጠበቅ ከመኸር ምርት ባሻገር በበጋ መስኖ ላይ በሰፊው መሥራት እንደሚጠበቅ አንስተዋል።
የመስኖ ልማትን ውጤታማ ለማድረግ ያሉ ጸጋዎችን በተገቢው መንገድ መጠቀም ያስፈልጋልም ብለዋል። ለዚህም በዕውቀት፣ በክህሎት እና የኅብረተሰቡን አሳታፊነት ባማከለ መንገድ ልዩ ትኩረት መስጠት ይገባል ነው ያሉት። ልማቱን ከነበረው ኋላቀር አሠራር ወደ ዘመናዊ ለማሻገር በርብርብ እንደሚሠራም ገልጸዋል።
የምዕራብ ጎጃም ዞን ምክትል አሥተዳዳሪ እና የግብርና መምሪያ ኀላፊ አጉማሴ አንተነህ በዘንድሮው የበጋ መስኖ ልማት ከ51 ሺህ በላይ ሄክታር መሬት በስንዴ፣ በአትክልት፣ በፍራፍሬ እና ሌሎች ልማቶች ይሸፈናል ብለዋል። 30 ሺህ ሄክታር መሬቱ በስንዴ እንደሚለማም ተናግረዋል። ከ380 ሺህ በላይ የአፈር ማዳበሪያ መቅረቡንም ጠቁመዋል።
በዞኑ ግንባታቸው የተጠናቀቁ ከስድስት በላይ የመስኖ ካናሎች ዝግጁ መኾናቸውንም አስታውቀዋል።
አስተያየታቸውን የሰጡ ተሳታፊዎች አስፈላጊ ዝግጅቶችን በማከናወን ቀድመው ወደ ሥራ መግባታቸውን ገልጸዋል።
ዘጋቢ ፦ ንጉስ ስንታየሁ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
