
በአማራ ክልል በኢሊኖ ተፅዕኖ በተፈጠረው የዝናብ እጥረት ሊፈጠር የሚችለው የምርት መጠን በመስኖ ልማት ለማካካስ የተለያዩ ተግባራት እየተከናወኑ ይገኛሉ።
በክልሉ በዋግ ኽምራ ብሔረሰብ አሥተዳደር ዝቋላ ወረዳ አሚኮ ያነጋገራቸው አርሶ አደሮች እንደተናገሩት በምርት ዘመኑ ኢሊኖ በፈጠረው ችግር የዝናብ እጥረት አጋጥሟቸዋል። ይህ የዝናብ እጥረት ለቀጣይም ስጋት እንደፈጠረባቸው አንስተዋል።
የአማራ ክልል አደጋ ስጋት ሥራ አመራር ኮሚሽን ኮሚሽነር ዲያቆን ተስፋው ባታብል በተፈጥሮ ዝናብ አጠር በኾኑ አካባቢዎች ጥናትን መሠረት በማድረግ መንግሥት አስፈላጊውን ፈጣን እና ተገቢ ምላሽ በመስጠት ላይ ይገኛል ብለዋል። ቀዳሚው ተግባር ማምረት በመኾኑ ፈጥነው የሚደርሱ ምርቶች እየተመረቱ ይገኛሉ ነው ያሉት።
ችግሩ ሊፈጠር እንደሚችል ቀድሞ በመታወቁም ጉዳት ለደረሰባቸው አካባቢዎች ፈጣን ድጋፍ ማድረስ እንዲቻል የተለያዩ የመጠባበቂያ ድጋፎች ቀድመው መዘጋጀታቸውን ገልጸዋል። በቀጣይ ቅንጅታዊ ሥራው ተጠናክሮ ይቀጥላል ነው ያሉት።
በማኅበረሰቡ በራስ አቅም ቅድሚያ የሚሰጡ የምላሽ ሥራዎች እንዲያከናወን እየተደረገ ነው ብለዋል።
በምክትል ርእሰ መሥተዳድር ማዕረግ የገጠር ዘርፍ አስተባባሪ ድረስ ሳህሉ (ዶ.ር) በክልሉ በኢሊኖ ተፅዕኖ
በዝናብ መዘገየት እና ቀድሞ መውጣት ምክንያት የሚታጣውን ምርት በከፍተኛ ደረጃ ለማካካስ አሁን ላይ በስፋት የውኃ እቀባ እና የማሠባሠብ ሥራዎች እየተከናወኑ ይገኛሉ ብለዋል።
በኤሊኖ ምክንያት የምርት እጥረት ሊያጋጥማቸው የሚችሉ አርሶ አደሮችን ለመደገፍ እና ከመንግሥት ድጋፍ በተጨማሪ “ከተረጅነት ወደ ምርታማነት” በሚል ሃሳብ ከ6ሺህ ሄክታር በላይ መሬት ምርት እየተሠበሠበ ይገኛል ነው ያሉት።
ተፅዕኖው በእንስሳት ሀብት ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ለመቀነስም እንስሳትን ውኃ እና መኖ ወደሚገኝባቸው አካባቢዎች የማዘዋወር፣ የመኖ ክምችት የማዘጋጀት እና የመጠባበቂያ እህል የማከማቸት ሥራዎች ተጠናክረው መሠራታቸውን አንስተዋል። የዝናብ እጥረት እና የኢሊኖ ተፅዕኖ ያለባቸውን አካባቢዎች ምላሽ ለመስጠት የሚያስችል በቂ እህል የማከማቸት ሥራ መሠራቱንም አንስተዋል።
እየተከናወነ ያለው ተግባር ውጤታማ መኾኑን ያነሱት አሥተባባሪው የተያዙት አቅጣጫዎች የዝናብ እጥረት ችግርን በዘላቂነት ለመፍታት የሚያስችሉ ተግባራት መኾናቸውን አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
