ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ የኾነችባቸውን የጦር ጄቶች ታጠቀች።

16
ኢትዮጵያ የመከላከያ ሠራዊቷን ዘመኑ በደረሰበት ቴክኖሎጂ እያጠናከረች፣ ለጠላቶቿ ስጋት፣ ለወገኖቿ ደግሞ ኩራት ኾናለች።
ሀገራዊ፣ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሁኔታዎች በፍጥነት እየተለዋወጡ ነው። የዓለም ፖለቲካ፣ ኢኮኖሚ እና ማኅበራዊ መልኮች በፈጣን ለውጥ ውስጥ ይገኛሉ። ዓለም በጂኦፖለቲካዊ እንቅስቃሴዎቿ ምክንያት መልክ እና ጠባይዋ ተቀያይሯል። አይገመቴነት የዘመን ዋነኛ መገለጫ እየኾነም ነው።
የአፍሪካ ቀንድ፣ የቀይ ባሕር ከባቢ፣ የፋርስ ባሕረ ሰላጤ፣ የአውሮፓ ጂኦፖለቲካ፣ የመካከለኛው ምሥራቅ አካሄድ በሁሉም አቅጣጫ በለውጥ ማዕበል እየተጎበኘ ነው። በአስገራሚው እና በአስፈላጊው የዓለም ክፍል በምሥራቅ አፍሪካ የቀይ ባሕር እና የሕንድ ውቅያኖስ በሚገናኙበት ልዩ ስፍራ ላይ የምትገኘው ኢትዮጵያ ለተለዋዋጩ የቀጣናው እንቅስቃሴ ራሷን እያዘጋጀች ነው።
ከጥንት ዘመን ጀምሮ የታላላቅ ኀያላን መራኮቻ በኾነው ቀጣና የምትገኘው ኢትዮጵያ በቀጣናው መሪ ኾና ለመገኘት የሚያስችላትን ሥራ እየሠራች ነው።
ራሷን በፖለቲካ፣ በኢኮኖሚ፣ በመከላከያ እና በደኅንነት ተቋማት አጠናክራለች። የውጭ ባዕዳዎች አና የውስጥ ባንዳዎች በጠላትነት የሚነሱባት ኢትዮጵያ አይደፈሬ መከላከያ ሠራዊት ገንብታለች። ሠራዊቱን በቴክኖሎጂ እያገዘች፣ ዘመኑን እየዋጀች የበለጠ እያሳደገችው እና አስፈሪ እያደረገችው ነው።
ከሩሲያ ጋር ጠንካራ ወዳጅነት ያላት ኢትዮጵያ ባደረገችው ስምምነት ዘመኑ የደረሰባቸውን የጦር ጄቶች ተረክባለች።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የሀገራችንን ሰላም እና ደኅንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል ነው ያሉት። ኢትዮጵያ በመከላከያ ኀይል እያደረገች ያለው ዝግጁነት ጥቃትን ቀድሞ ማስቀረት የሚያስችላትን አቅም እያላበሳት መኾኑን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም ከሩሲያ መንግሥት ጋር በተደረሰው ስምምነት መሠረት ዛሬ የመጀመሪያዎቹን 12 የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄቶች (Su-35 4++ Generation) መረከባቸውን አስታውቀዋል። በተጨማሪም አራት የኤስ-400 (S-400) የአየር መከላከያ ሥርዓት ባትሪዎችን ትረከባለች ብለዋል።
እነዚህን የጦር ጄቶች በመታጠቅ ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ኾናለች። ይህ ደግሞ ለኢትዮጵያ ልዩ ትርጉም አለው። ለቅርብ እና ለሩቅ ጠላቶቿ የሚሰጠው መልዕክትም አለ።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ እንደገለጹት ይህ ታሪካዊ ስኬት የኢትዮጵያን ሉዓላዊነት ይበልጥ የሚያጠናክር ነው። ወደፊትም የጋራ ደኅንነታችንን እና ቀጣናዊ መረጋጋትን ለማረጋገጥ የምናደርገውን ጉዞ በልበ ሙሉነት እንድንቀጥል ትልቅ አቅም ይኾነናል ነው ያሉት።
ከሮያል ዩናይትድ ሰርቪስ ኢንስቲትዩት የተገኘው መረጃ እንደሚያመላክተው የሱ-35 4ኛ++ ትውልድ የጦር ጄት የረቀቀ ቴክኖሎጂ የተገጠመለት፣ ፈጣን እንቅስቃሴ የሚያደርግ ሁለገብ ተዋጊ አውሮፕላን ነው።
ይህ አስደናቂ የጦር ጄት የመሬት እና የባሕር ላይ ዒላማዎችን ማጥቃት ይችላል። ረጅም ርቀት ተወንጫፊ መሳሪያዎችን የሚታጠቅ እና ሁለገብ ዒላማ የሚመታ ነው።
ኢትዮጵያ ከሰሃራ በታች ባሉ የአፍሪካ ሀገራት ቀዳሚ ኾና ይሄን የጦር ጄት መታጠቋ የቀጣናውን ሰላም እና ደኅንነት ለማረጋገጥ፣ የኀይል ሚዛንን ለማስጠበቅ እና የበላይ ለመኾን ያስችላታል።
✍️ በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሀገራችንን ሰላምና ደህንነት በዘላቂነት ለማረጋገጥ የምናደርገው ሁለንተናዊ ጥረት ዛሬ ሌላ አዲስ ምዕራፍ ላይ ደርሷል።
Next articleበዝናብ እጥረት ሊታጣ የሚችለውን ምርት በመሥኖ ለመተካት ምን እየተሠራ ነው ?