
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ወቅታዊ የሰላም እና የጸጥታ ሁኔታን በተመለከተ ከወጣቶች ጋር ውይይት አካሂዷል።
የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው እንደ ክልል እና እንደ ሀገር በትክክለኛው የልማት እና የዴሞክራሲ ሥርዓት ግንባታ ጎዳና ላይ እንገኛለን ብለዋል። ትላልቅ የልማት ሥራዎች እየተከናወኑ መኾናቸውንም አንስተዋል።
ባለፉት ሦስት ዓመታት በክልሉ የተፈጠረው የጸጥታ ችግር የልማት ሥራዎችን በሚፈለገው ልክ ለማከናወን እንቅፋት ኾኖ መቆየቱን አስታውሰዋል።
ወጣቶች የጥፋት ኃይሎችን ሴራ እና ዓላማ በመገንዘብ የተደቀነውን ፈተና መመከት ይገባቸዋል ነው ያሉት። የውስጥ እና የውጭ ጠላቶችን ሴራ በውል መረዳት እና የሰላም ዘብ መኾን እንደሚያስፈልግም አንስተዋል።
ነገ ማክሰኞ የሚካሄደውን የዋልያዎቹ እና የሴኔጋል ብሔራዊ ቡድን ጨዋታ በሰላማዊ መንገድ እንዲከናወን ማድረግ እንደሚገባም አስገንዝበዋል። ከተማዋን የቱሪዝም ከተማ ለማድረግ ትልቅ ዕድል መኾኑንም ገልጸዋል።
ጨዋታውን የስፖርታዊ ጨዋነት እሴትን በመላበስ መደገፍ እና በሰላም እንዲጠናቀቅ ማድረግ ይጠበቃል ነው ያሉት። ይህም ቀጣይ ሌሎች ጨዋታዎች እንዲከናወኑ ዕድል የሚሠጥ መኾኑን ነው የተናገሩት። ወጣቶች ኀላፊነታቸውን መወጣት እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል ።
የመድረኩ ተሣታፊ ወጣቶችም ሰላምን በማጽናት ሀገርን ለማስቀጠል ቁርጠኛ መኾናቸውን ገልጸዋል። በተለይም የከተማዋን ሰላም ለማስቀጠል ከሌሎች አካላት ጋር በቅንጅት እንደሚሠሩም ተናግረዋል።
#አሚኮ #ሰላም #ኢትዮጵያ 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም
✍️ ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
