
ቦሊቪያ በ19ኛው ክፍለ ዘመን ያጣችውን የባሕር በር ለማስታወስ እና የባለቤትነት መብት ጥያቄዋን ሕያው ለማድረግ በየዓመቱ እ.ኤ.አ. መጋቢት 23 ቀን ሕዝቧ “የባሕር ቀን” (Dia del Mar) እያለ በአንድነት በማክበር ጠንካራ ብሔራዊ መግባባትን ይፈጥራል።
ቦሊቪያን ኤክስፕረስ ዶት ኦርግ እንዳስነበበው መረጃ ቦሊቪያ እ.አ.አ በ1879 በተደረገው የፓሲፊክ ጦርነት በቺሊ ተሸንፋ የባሕር ዳርቻዋን አጣች። ብሔራዊ የባሕር በር የማግኘት ሕልሟን ለትውልድ ለማስተላለፍ ግን ዕለቱን በከፍተኛ ስሜት ታከብረዋለች። በትምህርት ሥርዓቷ ውስጥ የባሕር በር ጥያቄ የሀገሪቱ የሕልውና እና የማንነት ጉዳይ መኾኑን ከልጅነት ጀምሮ በስፋት ትሰብካለች።
ቦሊቪያን ጨምሮ የባሕር በር የሌላቸው ሀገራት ይህን ያህል ርብርብ የሚያደርጉት የባሕር በር ጥያቄ ከሀገር ደኅንነት፣ ከጂኦ-ፖለቲካዊ ተጽዕኖ ፈጣሪነት እና ከብሔራዊ ኩራት ጋር በእጅጉ የተቆራኘ በመኾኑ ነው።
የባሕር በር ለሀገራት የኢኮኖሚ ዕድገት፣ የውጭ ቀጥታ ኢንቨስትመንትን ለመሳብ እና የወጭ ንግድን ተወዳዳሪ ለማድረግ ያለው ድርሻ እጅግ የላቀ ነው።
የኢኮኖሚክስ ምሁሩ ፕሮፌሰር ጄፍሪ ሳክስ እና ባልደረቦቻቸው “የባሕር በር የሌላቸው ታዳጊ ሀገራት የሚገጥሟቸው ፈተናዎች” በሚለው ጥናታቸው የእነዚህ ሀገራት የትራንስፖርት እና ሎጂስቲክስ ወጭ ወደብ ካላቸው ሀገራት አንጻር በአማካይ ከ50 በመቶ በላይ የጨመረ ነው።
ይህ ከፍተኛ ወጭ የወጭ ንግድን በማዳከም ምርቶች በዓለም አቀፍ ገበያ ተወዳዳሪ እንዳይኾኑ ያደርጋቸዋል። የውጭ ባለሃብቶችም ትርፋማነታቸውን ለማረጋገጥ ሲሉ ወደብ ወዳላቸው ሀገራት እንዲያመሩ በማድረግ ኢንቨስትመንትን በእጅጉ ይጎዳል።
ፖል ኮሊየር “ዘ ቦተም ቢሊዮን” በተሰኘው መጽሐፋቸው የባሕር በር አልባነትን ከአስከፊ የድህነት ወጥመዶች አንዱ አድርገው የፈረጁት ለዚሁ ነው።
ትላልቅ ኢኮኖሚ እና የሕዝብ ቁጥር ያላቸው ሀገራት በጂኦ-ፖለቲካዊ ድርድር፣ በጋራ የኢኮኖሚ ትስስር እና የጋራ ተጠቃሚነትን መሠረት ባደረጉ ዲፕሎማሲያዊ ጥረቶች አሉታዊ ተጽዕኖውን በመፍታት አስተማማኝ የባሕር በር ተጠቃሚ መኾን ይችላሉ። ይህም በቀጥታ ሀገራዊ ምርትን በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ በማድረግ የውጭ ምንዛሬ ግኝትን ከፍ ለማድረግ ያስችላል።
የቦሊቪያ ታሪካዊ ክስተት ለኢትዮጵያ የባሕር በር ይገባኛል ጥያቄ ትልቅ የብሔራዊ ትርክት ግንባታ እና የትውልድ ቅብብሎሽ ትምህርት ይሰጣል።
ቦሊቪያ ከአንድ ምዕተ ዓመት በላይ የባሕር በር ብታጣም ጥያቄውን በሕዝብ ልብ ውስጥ በማቆየት የሀገራዊ አንድነት መፍጠሪያ አድርጋው ቀጥላለች። የኢትዮጵያም የባሕር በር ጉዳይ የፖለቲካ ልሂቃን አጀንዳ ብቻ ሳይኾን በመላው ሕዝቡ ዘንድ በጋራ መግባባት ላይ የተመሠረተ ቋሚ የትኩረት አቅጣጫ ኾኖ ሊቀጥል ይገባል።
በአሁኑ ወቅት ኢትዮጵያውያን የባሕር በር ማግኘትን እና ወደ ቀይ ባሕር መመለስን የሕልውናቸው ጉዳይ አድርገውታል። ሕዝቡ የሀገሪቱን የባሕር በር ፍላጎት ከታሪክ ባለቤትነት እና ከተገቢነት አኳያ በመመዘን ከመንግሥት ጎን መቆሙንም በተግባር እያረጋገጠ ይገኛል።
በማንኛውም ሀገር የባሕር በርን የማረጋገጥ ጉዞ ስኬታማ የሚኾነው ምሁራን በተጨባጭ ምርምር፣ ዲፕሎማቶች በሰላማዊ ድርድር፣ ሕዝቡም በአንድነት እና በጽናት ከመንግሥት ጎን በመቆም የጋራ የኢኮኖሚ እና የሉዓላዊነት ትርክታቸውን ከግብ ለማድረስ በቅንጅት ሲሠሩ ብቻ ነው።
#ባሕር_በር #ሕልውና #ኢትዮጵያ #አሚኮ🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_18_2019_ዓ_ም
በስማቸው አጥናፍ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
