
የታሪክ መጻፊያ ብዕር፣ የታላቅ ሀገር የጋራ ዜማ መዝሙር፣ የጀግንነት መነሻ፣ የኀያልነት መዳረሻ፣ የመከራ ቀን ማለፊያ፣ የማዕበል ዘመን መቅዘፊያ፣ የሁልጊዜ መኩሪያ፣ የታላቅ ሕዝብ ማስተሳሰሪያ ገመድ ነው።
እናት ሀገሩን ልድፈር ወደ አለው ሳንጃ ስቦ ጦር ይሰብቃል። መነሻው የሀገር ፍቅር፣ መዳረሻው የሀገር ክብር ነው። ደልቶት አይኖርም፣ ተዝናንቶ አያድርም፣ ማደሪያው ምድር ቆፍሮ፣ ምግቡ ኮቸሮ፣ ለሕይወቱ አይሳሳም፣ ውድ ሀገሩን አያስነካም ጀግናው ወታደር።
ወታደር ታሪክ በደም የሚፃፍበት ብዕር፣ ኮርተው የሚናገሩለት ዝና፣ ከዘመን ዘመን የሚዜምበት ዜማ ነው። ጀግንነት በሚበዛበት የኢትዮጵያ ታሪክ ውስጥ ደመቅ ያለው የወታደር ነው። ጦረኛ ኢትዮጵያዊ ባይኖር፣ የማያወላውል ጀግና በምድሯ ባይፈጠር ዓድዋ ተራራ እንጂ ድል ባልኾነ ነበር። የአፍሪካ ምድርም በጨለማ በኖረ ነበር። ኢትዮጵያን እንገዛለን፣ ኢትዮጵያውያንን እናስገብራለን፣ ኢትዮጵያዊነትን እናጠፋለን ያሉት ሁሉ በጀግና ልጆቿ ጠፍተዋል።
የኢትዮጵያውያን ቁጣ መብረቅ ነው አድርቆ የሚጥል፤ ምትሃት ነው ከሥሩ የሚነቅል፤ ረቂቅ መንፈስ ነው ነብስን ከሥጋ የሚነጥል፣ በዘመናት ቅብብል ኢትዮጵያን አጠፋለሁ ያለ የጠላት ማዕበል በወታደር ተመልሷል፣ ለኢትዮጵያውያን ይሁን የተባለ የክፋት ፅዋ ከድንበር ማዶ ፈስሷል። የተቆለለ የጠላት ገደል ፈራርሷል። ትዕቢት የገፋው ጠላት ሁሉ የኢትዮጵያውያንን ክንድ ቀምሷል።
ኢትዮጵያዊነት ማሸነፊያ፣ ኢትዮጵያዊነት የጨለማን ዘመን ማለፊያ፣ ኢትዮጵያዊነት ኩራት፣ ኢትዮጵያዊነት ጽናት፣ ኢትዮጵያዊነት ቀዳሚነት፣ ኢትዮጵያዊነት አይለወጤነት፣ ኢትዮጵያዊነት የድል ምልክት፣ ኢትዮጵያዊነት የመልካም ነገር ተምሳሌት ነውና። ከኢትዮጵያዊነት ላይ ውትድርና ሲጨመርበት ደግሞ ግርማው ልዩ ነው። የዓድዋ የድል ጥላ፣ የአምስት ዓመቱ የአርበኝነት መላ፣ ጠላት የማይፈታው ቀመር፣ የማይመረምረው ምስጢር፣ ኢትዮጵያዊ የማያወልቀው ዘላለማዊ ክብር ነው።
ኢትዮጵያውያን በራስ ትጥቅ እና ስንቅ እየዘመቱ ማንነት እስከነ ክብሩ፣ ሀገር እስከ ድንበሩ አቆይተዋል። የቀደሙት ኢትዮጵያውያን ሲያልፉም የማይሻር፣ የማይረሳ ቃል ኪዳን አደራ ብለዋል፣ ልጆቻቸውን በቃል ኪዳን አስረዋል። ቃል ኪዳን ያሰራቸው፣ የአባቶቻቸው የጀግንነት ታሪክ ያላስተኛቸው፣ የኢትዮጵያዊነት ፍቅር የዋጃቸው፣ የሀገር ክብር የጠራቸው ጀግና ልጆች ዛሬም እንደ ትናንቱ “እማማ ሆይ አለንልሽ፣ እኛ እያለን ክብርሽም ስምሽም ዝቅ አይልም” እያሉ ነው።
ድሎት ሳያምራቸው፣ የወገን ናፍቆት ወደኋላ ሳይጎትታቸው፣ መከራ ሳያደክማቸው፣ ቁሩ እና ሀሩሩ ሳይበግራቸው፣ ለእማማ ኢትዮጵያ ምቾትን እና ሕይወትን ሰጥተው ይኖራሉ። ስለ እርሷ ሲሉ ይኖራሉ፣ ስለ እርሷም ያልፋሉ። በስሟ ምለው፣ ለቃሏ ታምነው፣ ለክብር ብለው መሪር ጽዋን ይቀምሳሉ፣ ክፉ ቀንን ይታገሳሉ።
“እኔ ላገሬ አደራ አለብኝ፣
ጎጆ ትዳሩም ከዚያው ይቅርብኝ፣
ሀገሬን ጠላት ከሚደፍርብኝ፣
ድንበር ዘምቸ ከሠንደቋ ሥር መሞት አለብኝ” እንደተባለ ሁሉም ነገር ይቅርብኝ ብለው ለሀገር ማገር፣ ለወገን ክብር ሊኾኑ ጽኑ ቃል ኪዳን ያስራሉ።
ተድላ ዘዮሐንስ የኢትዮጵያ ታሪክ ኢጣሊያ በኢትዮጵያ በተሰኘው መጽሐፋቸው የታሪክ ጸሐፊዎች፣ ባለቅኔዎች እና መንግሥታት ኢትዮጵያን በየዘመናቱ በተለያዩ ስሞች ሊጠሯት ይችላሉ፤ በተለያየ ስም የምትጠራው ኢትዮጵያ ለዘመናት በልጆቿ ጀግንነት እና አይበገሬነት ነጻነቷን እና ሉዓላዊነቷን አጽንታ የኖረች መኾኗን ጽፈዋል፡፡ እርሷ በኢትዮጵያዊነቷ ኖራለች፣ ትኖራለችም ብለዋል፡፡
“የውጭ ወራሪዎች ኢትዮጵያን ለማጥቃት እና ለመያዝ ሞክረዋል፡፡ ሁሉም በኢትዮጵያውያን ድል እየተመቱ ወደመጡበት ተመልሰዋል” ነው የሚሉት።
እነሆ ዛሬም ኢትዮጵያ በልጆቿ ጀግንነት ትጠበቃለች፤ በልጆቿ አንድነት ትጸናለች፤ ጠላቶቿን ድል እየነሳች ከዘመን ዘመን ትሸጋገራለች።
#የመደመር_መንግሥት!
#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_17_2019_ዓ_ም
በታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
