
በዓባይ ወንዝ ላይ የኢትዮጵያን የዘመናት ሕልም እውን በማድረግ በጉባ ሰማይ ስር ግዙፉን ሰው ሠራሽ ሐይቅ የፈጠረው ትውልድ ዛሬም ታሪክን በድጋሚ ለመጻፍ ጉዞውን ጀምሯል።
የታላቁ የኢትዮጵያ ሕዳሴ ግድብ ድል ኢትዮጵያ የማይቻለውን ማድረግ እንደምትችል ያረጋገጠችበት፣ የራሷን የውኃ ዓለም የፈጠረችበት ትውልዳዊ ምዕራፍ ነው።
ዛሬም ኢትዮጵያን ከኃያላኖቹ ተርታ ለማሰለፍ በሚደረገው ብሔራዊ ጥረት ውስጥ ወሳኝ የኾነውን የባሕር በር ፍላጎት እውን ለማድረግ ጉዞውን ጀምሯል። ይህ ጉዞ የሌሎችን መብት የሚጋፋ ሳይኾን የኢትዮጵያን ተፈጥሯዊ እና ታሪካዊ መብት ከማስከበር የሚመነጭ የሕልውና ጥያቄ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ኢትዮጵያ በጂኦግራፊ ብቻ የታሰረች ሳትኾን ከቀይ ባሕር ጋር ያላት ታሪካዊ፣ ጂኦፖለቲካዊ እና ኢኮኖሚያዊ ትስስር ሊታለፍ የሚችል አይደለም ማለታቸው ይታወሳል።
የባሕር በር ጥያቄው የሰላም፣ የልማት እና የጋራ ተጠቃሚነት እንጂ የማንም ሉዓላዊነት ላይ የሚቀጣ ዛቻ እንዳልኾነ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ጠቁመዋል።
ከወደብ ባለቤቶች ጋር በንግድ፣ በኢንቨስትመንት እና በጋራ ዕድገት ላይ ተመስርቶ በሰላማዊ መንገድ የባሕር ተጠቃሚነቷን ታረጋግጣለች፤ ይህ የማይቀር የኢትዮጵያ የታሪክ አቅጣጫ እንደኾነም አጽንኦት ሰጥተዋል።
በዓባይ ላይ የጣና ሐይቅን ከሁለት እጥፍ በላይ ውኃ የያዘውን፣ 150 ሜትር ጥልቀት እና 240 ኪሎ ሜትር ርዝመት ያለውን ሐይቅ የገነባው ሕዝብ በቀይ ባሕር ማዕበል ውስጥ የራሱን መርከብ አሰማርቶ የኢኮኖሚ ነጻነቱን ለማረጋገጥ ቆርጦ ተነስቷል።
የባሕር በር ማግኘት ማለት የንግድ መስመሮችን ማስጠበቅ፣ የምርት ውድድር አቅምን ማሳደግ እና ለቀይ ባሕር አካባቢ ሰላም እና መረጋጋት አስተማማኝ አጋር መኾን ማለት ነው።
በታሪክ ውቅያኖስ ውስጥ የገጠሟትን ፈተናዎች ሁሉ በድል አድራጊነት ማለፍ የለመደችው ኢትዮጵያ የዛሬው ትውልድ በሠለጠነ ዲፕሎማሲ፣ በኢኮኖሚ አቅም እና በጸና የዓላማ ቁርጠኝነት የባሕር በር ርዕይዋን ከግብ ለማድረስ ዝግጁነቱን አረጋግጧል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
