የመከላከያ ሠራዊት ጥብቅ ሥነ ምግባርን፣ ዓለም አቀፋዊነትን እና ጠንካራ ተቋማዊ ቁመናን ገንብቷል።

7
የአንድ ሀገር ሉዓላዊነት እና ዘላቂ ሰላም አስተማማኝ የሚኾነው በዘመናዊ ዕውቀት፣ በሕዝባዊ ወገንተኝነት እና በጥብቅ ሥነምግባር የታነጸ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት ተቋም ሲኖር ነው። የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት ደግሞ እነዚህ ዘርፎች ላይ ትኩረት በማድረግ የተለያዩ ሥራዎችን ሲሠራ ቆይቷል። አሁንም እየሠራ ይገኛል። ሠራዊቱ የሀገርን ሉዓላዊነት ከመጠበቅ ባለፈ በዓለም አቀፍ ደረጃ የሚጠበቅበትን ሚና ለመወጣት የሚያስችሉትን ሦሥት ምሰሶዎች ገንብቷል።
👉የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ጥብቅ ሥነምግባር እና ሙያዊ ብቃትን ገንብቷል። ሠራዊቱ ከማንኛውም የፖለቲካ ወገንተኝነት ነጻ ኾኖ ሀገርን እና ሕዝብን ብቻ የማገልገል ጥብቅ ወታደራዊ ሥነምግባር የተላበሰ ስለመኾኑም በተለያዩ ጊዜያት ይነገራል፤ ሠራዊቱም በተግባር ቀን ከቀን
እየገለጠው ነው። በትዕዛዝ ሰንሰለት መመራት፣ በሕገ መንግሥታዊ ታማኝነት እና በሰብዓዊ መብቶች አያያዝ ዙሪያ ከፍተኛ ጥንቃቄ እንደሚያደርግም መረጃዎች ያመላክታሉ። የጎዱትን ተንከባክቦ፣ የካዱትን በፍቅር ይዞ ወደሰላም ያመጣል። ይህ ጥብቅ ሥነ ምግባር ሠራዊቱ በማንኛውም አስቸጋሪ የኾነ ግዳጅ ውስጥ ሕዝባዊ አመኔታን ሳያጣ በስኬት እንዲወጣ ማስቻሉንም ይገልጻሉ።
👉የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ዓለም አቀፋዊነት እና የሰላም ማስከበር ተሳትፎ ላይም በጉልህ የሚጠቀሱ ታሪኮችን አስመዝግቧል። በተለያዩ ጊዜዎች የወጡ የውጭ ጉዳይ ሚኒስቴር መግለጫዎች እንደሚያመላክቱት የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት በሀገር ውስጥ ብቻ የተወሰነ ሳይኾን በአፍሪካ እና በዓለም አቀፍ ደረጃ በሰላም ማስከበር ዘርፍ ትልቅ ስም እና ልምድ ያካበተ ነው።
በተባበሩት መንግስታት እና በአፍሪካ ኅብረት የሰላም ማስከበር ተልዕኮዎች ላይ ግንባር ቀደም በመኾን ሠራዊቱ በሶማሊያ፣ ሱዳን ቀደም ባሉት ጊዜም በኮሪያ እና ላይቤሪያ ታላቅ ስም እና አድናቆት አትርፏል። በምሥራቅ አፍሪካም በሶማሊያ እና በደቡብ ሱዳን ቀጣናዊ ሰላም እና መረጋጋትን ለመጠበቅ፣ ሽብርተኝነትን ለመዋጋት እና ድንበር ተሻጋሪ ስጋቶችን ለመቀልበስ ሲያደርግ የነበረው ተሳትፎ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ ዘንድ ከፍተኛ ዕውቅና እንዲሰጠው አድርጎታል።
👉የሀገር መከላከያ ሚኒስቴር ዓመታዊ የሥራ አፈጻጸም ሪፖርቶች እንደሚያስረዱት በኢትዮጵያ ጠንካራ የመከላከያ ሠራዊት ተቋም ተገንብቷል። ሠራዊቱም በሰው ኀይል፣ በቴክኖሎጂ እና በትጥቅ ረገድ የማዘመን ሥራ ሲሠራ ቆይቷል። አሁንም በከፍተኛ ትኩረት እየተሠራ ይገኛል። ወታደራዊ
የትምህርት እና የሥልጠና ተቋማት ዘመናዊ እና ሳይንሳዊ ዕውቀትን እንዲሁም ቴክኖሎጂን መሠረት ባደረገ መልኩ እንዲደራጁ ተደርገዋል። ይህም ሠራዊቱ የአየር፣ የምድር እና የሳይበር ደኅንነትን በአስተማማኝ ሁኔታ ለመጠበቅ የሚያስችል ጠንካራ ተቋማዊ መዋቅር እንዲገነባ አግዞታል።
በጥቅሉ እነዚህ መረጃዎች የሚያረጋግጡት የኢፌዲሪ መከላከያ ሠራዊት በጥብቅ ሥነምግባር የታነጸ ቀጣናዊ እና ዓለም አቀፋዊ ሚናውን በብቃት የሚወጣ እና በዘመናዊ ዕውቀት ላይ የተመሠረተ ጠንካራ ተቋማዊ ቁመና ያለው ኀይል መኾኑን ነው። ይህ ዓይነቱ የተቋም ግንባታ የሀገርን የረጅም ጊዜ ደኅንነት እና ልማት በጽኑ መሠረት ላይ ለመጣልም ወሳኝ ሚና ይጫወታል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleኢልኒኖ ከሥጋት አልፏል?