ኢልኒኖ ከሥጋት አልፏል?

13
ባሕር ዳር: ጥቅምት 17/2019 ዓ.ም (አሚኮ) ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ድርጅት የኢልኒኖ አደጋ ሊከሰት እንደሚችል ሲያስጠነቅቅ ቆይቷል።
ጥቅምት 11/ 2019 ዓ.ም ዓለም አቀፉ የአየር ንብረት ድርጅት እና የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት የሰብአዊ ጉዳዮች ማሥተባበሪያ ቢሮ በጋራ ባወጡት ጋዜጣዊ መግለጫ ግን አደጋው መከሰቱን አረጋግጠዋል።
በመግለጫው ኢልኒኖ ከሥጋት አልፎ አኹን በእርግጥም አደጋው ተፅዕኖ ማሳደር ጀምሯል ተብሏል። አኹን ያለው የኢልኒኖ የሙቀት መጠን እና ጥንካሬ ባለፉት አራት አስርት ዓመታት ከተመዘገቡት መለኪያዎች ሁሉ በላይ መኾኑ ተነግሯል። የክስተቱ የጉዳት መጠን በፈረንጆች 2026 ማጠናቀቂያ ላይ ከፍተኛ ጫፍ ይደርሳል።
ከ2027 አዲስ ዓመት ጀምሮ የአየር ንብረት ክስተቱ መረጋጋት ቢጀምርም በምግብ ዋስትና እና በሰብአዊ ህይወት ላይ ያሳደረው ተጽዕኖ ግን ለረጅም ጊዜ ይዘልቃል ተብሏል።
​✍️በመግለጫው የተነሱ ዋና ዋና ሃሳቦች፦
#የውቅያኖስ ሙቀት መጨመር፦ ከኅዳር እስከ ጥር 2019 ዓ.ም ባሉት ወራት (በፈረንጆች ከኖቬምበር 2026 እስከ ጃንዋሪ 2027) የፓሲፊክ ውቅያኖስ የላይኛው የውኃ አካል ሙቀት ከመደበኛው በላይ በ3.8 ዲግሪ ሴልሺየስ ይጨምራል።
​#የአየር ንብረት መዛባት፦ ምሥራቅ አፍሪካ፦ ከጥቅምት እስከ ታህሳስ 2019 ዓ.ም ባለው የዝናብ ወቅት ከመደበኛው በላይ የኾነ ከፍተኛ ዝናብ ይጥላል። ይህም የጎርፍ አደጋን ያመጣል።
​ደቡባዊ አፍሪካ፡- ከኅዳር 2019 ዓ.ም ጀምሮ ድርቅ ይከሰታል። ይህም የሰብል ምርትን እና የውኃ አቅርቦትን ይጎዳል። ​ደቡብ ምሥራቅ እስያ፦ የሙቀት መጠን ይጨምራል፦ የዝናብ እጥረት ይከሰታል። የደኖች ቃጠሎ ሥጋትም ያጋጥማል።
​የአሜሪካ አህጉራት፦ በሰሜን ምዕራብ አሜሪካ እና በደቡብ አሜሪካ ክፍሎች ከፍተኛ ዝናብ እና ጎርፍ ይከሰታል። በማዕከላዊ አሜሪካ እና በአማዞን አካባቢዎች ደግሞ የድርቅ ሥጋት ይፈጠራል።
​✍️የቅድመ ጥንቃቄ ጥሪ፦ ​ድርጅቶቹ ወቅታዊ የአየር ንብረት ትንበያዎችን ወደ ተግባራዊ ውሳኔ ለመቀየር በጋራ እየሠሩ መኾኑን በጋራ መግለጫው ተመላክቷል።
መንግሥታት እና ሰብአዊ ድርጅቶች ደግሞ አደጋው ከመከሰቱ በፊት አስቸኳይ የቅድመ ጥንቃቄ እርምጃዎችን መውሰድ እንደሚገባ አሳስበዋል።
የአሚኮ ዲጅታል ቤተሰብ ይኹኑ!
ለኅብረተሰብ ለውጥ እንተጋለን!
Previous article“የውጭ ባዕዳ እና የውስጥ ባንዳዎች ተላላኪ ልንኾን አንችልም” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች
Next articleየመከላከያ ሠራዊት ጥብቅ ሥነ ምግባርን፣ ዓለም አቀፋዊነትን እና ጠንካራ ተቋማዊ ቁመናን ገንብቷል።