“የውጭ ባዕዳ እና የውስጥ ባንዳዎች ተላላኪ ልንኾን አንችልም” የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች

11
ለዓመታት የቀጠለ ግጭት ሕዝብን በእጅጉ ጎድቷል። በአማራ ክልል ባለፉት ዓመታት በተፈጠረው ግጭት ሕይወት ጠፍቷል፤ ንብረት ወድሟል፤ የሕዝብ ማኅበራዊ ግንኙነት ተጎድቷል፤ ሕጻናት እና ታዳጊዎች ከትምህርት ገበታ ርቀዋል። ለዓመታት የተገነቡ ተቋማትም ወድመዋል፤ ተጎድተዋል።
የክልሉ ሕዝብ ለብዝበዛ ተዳርጓል፤ ከማኅበረሰቡ እሴት እና ባሕል ያፈነገጡ አስነዋሪ ተግባራት ተፈጽመዋል። ማኅበረሰቡ ለከፍተኛ የሥነ ልቦና ጫና ተዳርጎ ቆይቷል። ለዓመታት የዘለቀው ግጭት ክልሉ በማኅበራዊ፣ በኢኮኖሚ እና በፖለቲካዊ ጉዳዮች ዋጋ እንዲከፍል አድርጓል። ይህ ግጭት ክልሉ በሙሉ አቅሙ ወደ ልማት እንዳይገባ፣ ውድድር በበዛበት ዘመን እምቅ አቅሙን አውጥቶ እንዳይወዳደር እንቅፋት ኾኖበት ቆይቷል።
ይህን ግጭት ለመቋጨት ተደጋጋሚ ጥረቶች ተደርገዋል። መንግሥት የክልሉ ግጭት እንዲቆም፤ የተረጋገጠ ሰላም እንዲፈጠር ተደጋጋሚ የሰላም አማራጮችን አቅርቧል። ለውይይት እና ለንግግር በሩን ከፍቷል። በጫካ የነበሩ በርካታ ታጣቂዎች የቀረበውን የሰላም አማራጭ ተቀብለዋል።
በግጭት እና በጦርነት የሚፈታ የሕዝብ ጥያቄ የለም በማለት ሰላምን አስቀድመዋል፤ መሣሪያቸውን አስቀምጠው ሰላማዊ ትግልን መርጠዋል። ይሄን በማድረጋቸውም የክልሉ ሰላም ከጊዜ ወደጊዜ እየተሻሻለ እንዲሄድ እና ማኅበረሰቡ እንዲያርፍ አድርጓል።
ከሰሞኑ የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች እርስ በእርስ መጠፋፋት ምንም ፋይዳ የለውም፤ እርስ በእርስ መጠፋፋት ማብቃት አለበት ብለዋል። ግጭት ለውጥ እንደማያመጣ፣ ማብቃትም እንዳለበት በማመን የሰላም አማራጭን ተቀብለናል ነው ያሉት።
“የውጭ ባዕዳ እና የውስጥ ባንዳዎች ተላላኪ ልንኾን አንችልም፤ የውጭ ባዕዳ እና የውስጥ ባንዳ ሀገር ለማፍረስ የሚሠሩ ናቸው” ብለዋል። የሰላም አማራጭን የተቀበሉ ታጣቂዎች የበደልነውን ሕዝብ ለመካስ ዝግጁ ነን ነው ያሉት።
የሃሳብ ልዩነትን በመሣሪያ ለማሸነፍ ያደረጉት ትግል የወንድማማች መገዳደልን ከመፍጠር፣ ኅብረተሰብን ለስቃይ ከመዳረግ እና ንብረት ከማውደም ውጭ ያመጣው ትርፍ አለመኖሩንም ገልጸዋል።
ትርፍ ያለው ከሰላም፣ ከፍቅር እና ችግሮችን በውይይት ከመፍታት መኾኑንም አንስተዋል። መንግሥት እያደረገ ያለውን የሰላም ጥሪ አጠናክሮ እንዲቀጥል እና ሌሎች በጫካ የሚገኙ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን እንዲቀበሉም ጠይቀዋል።
የአማራ ክልል ርእሰ መሥተዳድር አረጋ ከበደ በ12ኛው የጣና ከፍተኛ የአፍሪካ ጸጥታ ፎረም ላይ ባደረጉት ንግግር ሰላም የሚሰፍነው በአዋጅ አይደለም ብለዋል። ሰላም የሚሰፍነው ተግባራዊ ርምጃዎች ሲኖሩ መኾናቸውን አመላክተዋል። ሰላም እና ልማት የማይነጣጠሉ መኾናቸውን እንገነዘባለን ነው ያሉት። የአማራ ክልል ሰላምን ለማረጋገጥ እየተሠራ መኾኑንም ተናግረዋል።
ግጭት አውዳሚ ነው፤ በግጭት ሕዝብ እና ሀገር ይከሥራሉ፤ ሕዝብ እና ሀገር የሚጠቀሙት ከሰላም ነው፤ ለሀገር የሚያስብ፣ የባንዳዎችን እና የባዕዳዎችን ሴራ የሚረዳ፣ የሕዝብ ሰላም እጦት የሚያሳስበው ሁሉ የሰላም አማራጭን መቀበል አለበት፤ በዚህ ዘመን ሰላም እና ውይይት የጀግኖች ምርጫ ናቸው፤ ከሰላም እና ውይይት ውጭ ያሉ አካሄዶች ለዘመኑ የሚመጥኑ አይደሉም ብለዋል።
ዘጋቢ:- ታርቆ ክንዴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“ደማችሁ ደማችን፣ አጥንታችሁ አጥንታችን፣ ድላችሁም የኢትዮጵያ ነው” ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው
Next articleኢልኒኖ ከሥጋት አልፏል?