
በባሕር ዳር ከተማ የመከላከያ ሠራዊትን የሚደግፍ እና የኢትዮጵያን ጠላቶች የሚያወግዝ ሕዝባዊ ሰላማዊ ሰልፍ ተካሂዷል።
በመርሐ ግብሩ መልዕክት ያስተላለፉት የባሕር ዳር ከተማ አሥተዳደር ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባ ጎሹ እንዳላማው የኢትዮጵያ ታሪክ ከነጻነት እና ከተጋድሎ ጋር የተያያዘ መኾኑን ገልጸዋል። ዛሬም የሀገር ምልክት ለኾነው የሀገር መከላከያ ሠራዊት ድጋፋችንን ስንገልጽ ዳግም በሰንደቅ ዓላማችን ፊት ቃል እየገባን፣ የሠራዊቱን የምንጊዜም ጀግንነት እያረጋገጥን ነው ብለዋል።
የኢትዮጵያ መከላከያ ሠራዊት ሀገራችንን ከውጭ ጠላቶች እየተከላከለ፤ የውስጥ አፍራሽ ኃይሎችንም እየመከተ ሀገር እንዲትጸና እያደረገ ዘልቋል ነው ያሉት። በአሁኑ ወቅትም የውጭ ባዳዎች እና የውስጥ ባንዳዎች ሀገር ለማፍረስ እያደረጉት ያለውን ተልዕኮ በመመከት ሀገር የማጽናት ተልዕኮውን በጀግንነት እየተወጣ መኾኑን አንስተዋል።
የመከላከያ ሠራዊቱ ከሕዝብ የወጣ የሕዝብ ልጅ ነው ያሉት ተቀዳሚ ምክትል ከንቲባው የባሕር ዳር ሕዝብ ድጋፉን የሚገልጸውም ለዚህ ማረጋገጫ ነው፤ ከዚህ አደባባይ የወጣነውም ከሠራዊቱ ጋር አብረን መኾናችንን ለመግለጽ ነው ብለዋል።
ለሀገር መስዋዕትነት እየከፈለ ለሚገኘው ለመከላከያ ሠራዊቱ ባስተላለፉት መልዕክት “ደማችሁ የደማችን፣ አጥንታችሁ አጥንታችን፣ ድላችሁም የኢትዮጵያ ነው፤ ሁልጊዜም ከጎናችሁ መኾናችንን እናረጋግጣለን” ብለዋል።
የሀገራዊ ርዕያችን እና መሻታችን የሚሳካው በውስጣዊ አንድነት ነው ብለዋል። ለዚህም እስከ አሁን የቆየው የደም መፋሰስ መንገድ ሊቆም እና ለሰላም መቆም እንደሚገባም ገልጸዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
