የሚኒስትሮች ምክር ቤት በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ውሳኔ አሳለፈ።

43

 

የሚኒስትሮች ምክር ቤት ዛሬ ባካሄደው 59ኛ መደበኛ ስብሰባ በተለያዩ ጉዳዮች ላይ ተወያይቶ ውሳኔ አሳልፏል፡፡

1. ምክር ቤቱ በቅድሚያ የተወያየው የአስፈጻሚ አካላትን አደረጃጀት፣ ሥልጣን እና ተግባር ለመወሰን በቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ሕገ መንግሥት እና ምርጫ ሕግ በየአምስት ዓመቱ የሚደረገውን ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ በሕገ መንግሥቱ አንቀጽ 56 መሰረት አዲስ የአስፈጻሚ አካላት ሥልጣን እና ተግባር ማደራጀት የሚጠበቅ በመኾኑ በ2018 ዓ.ም በተደረገው ሀገራዊ ምርጫ ተከትሎ የፌዴራል አስፈጻሚ አካላትን በአዲስ መልክ ለማቋቋም እንዲያስችል ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ አዋጁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

2. ቀጥሎም ምክር ቤቱ የተወያየው ብሔራዊ የዳታ አሥተዳደር ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

የኢትዮጵያ የዲጂታል ትራንስፎርሜሽን ግቦችን ለማሳካት፣ የዳታ ደኅንነትን እና ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ፣ የዳታ መጋራትን፣ የዳታ ተናባቢነትን እና የዳታ መልሶ አጠቃቀምን በማጠናከር የመንግሥት አገልግሎቶችን ለማዘመን፣ የአርቲፊሻል ኢንተለጀንስ ምርምርና የፈጠራ አቅምን ለማጎልበት፣ የኢኖቬሽን እና የዲጂታል ኢኮኖሚ እድገትን ለማፋጠን እና በዳታ የተመራ የኢኮኖሚ ልማት ሥርዓት ለመገንባት እንዲያስችል ረቂቅ አዋጁ ተዘጋጅቶ ለሚኒስትሮች ምክር ቤት ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቁ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

3. ከዚያም ምክር ቤቱ የተወያየው ከዓለም አቀፍ የልማት ማኅበር ጋር በተፈረመው ለኃይል ሴክተር ሪፎርም፣ ኢንቨስትመንት እና ዝመና ምዕራፍ አንድ ፕሮጀክት ማስፈጸሚያ የሚውል የአንድ መቶ አርባ አምስት ሚሊዮን ስምንት መቶ ሺ ኤስ.ዲ.አር ብድር ስምምነት ማጽደቂያ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ምክር ቤቱም ስምምነቱ ከሀገራችን የብድር ፖሊሲ ጋር የሚጣጣም መኾኑን በማጋገጥ ረቂቅ አዋጁ ለሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

4. የፌዴራል ገቢ ግብር ማሻሻያ ደንብ ሌላው ምክር ቤቱ የተወያየበት አጀንዳ ነው፡፡

ደንቡ የፌዴራል የገቢ ግብር ግልጽነትን እና አሥተዳደራዊ ቅልጥፍናን ለማረጋገጥ እና ከተሻሻለው የፌዴራል ገቢ ግብር አዋጅ ቁጥር 979/2008 ጋር የተጣጣመ እንዲኾን ለማድረግ እንዲቻል የተሻሻለውን የሚኒስትሮች ምክር ቤት የገቢ ግብር ደንብ ቁጥር 410/2009 እንደገና ማሻሻል አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በሥራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

5. ምክር ቤቱ የፌዴራል ተጨማሪ እሴት ታክስ ማሻሻያ ደንብ ላይ ተወያይቷል፡፡

ቀደም ሲል የሙያ አገልግሎት እና ሌሎች አቅርቦቶችን እየሰጡ የተርን ኦቨር ታክስ ይሰበስቡ የነበሩ ግብር ከፋዮች የተርን ኦቨር ታክስ የተሻረ በመኾኑ እነዚህ ግብር ከፋዮች ለተጨማሪ እሴት ታክስ ተመዝግበው ታክሱን እንዲሰበስቡ ለማድረግ፣ በአንዳንድ አቅርቦቶች ላይ የተጣለው ታክስ ለኅብረተሰቡ በሚቀርቡ መሰረታዊ አቅርቦቶች እና በሀገር ውስጥ ኢንዱስትሪዎች ተወዳዳሪነት ላይ ጫናን ያሳደረ በመኾኑ አቅርቦቶቹን ከታክሱ ነፃ ለማድረግ እንዲያስችል ማሻሻያ ደንቡ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በረቂቅ ደንቡ ላይ በሰፊው ከተወያየ በኋላ ግብአቶችን በማከል በፌዴራል ነጋሪት ጋዜጣ ታትሞ ከወጣበት ቀን ጀምሮ በስራ ላይ እንዲውል በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

6. በመጨረሻም ምክር ቤቱ የተወያየው የመከላከያ ሠራዊት አዋጅን ለማሻሻል የቀረበ ረቂቅ አዋጅ ላይ ነው፡፡

ተቋሙ በኢ.ፌ.ዴ.ሪ ህገ መንግሥት አንቀጽ 87 ድንጋጌዎች መሰረት የተሰጡትን ሀገራዊ ተልዕኮዎች በሕግ አግባብ ለመፈፀም እንዲችል የመከላከያ ሠራዊት አዋጅ ቁጥር 1286/2015 ማሻሻል አስፈላጊ ኾኖ በመገኘቱ ረቂቁ ተዘጋጅቶ ለምክር ቤቱ ቀርቧል፡፡

ምክር ቤቱም በጉዳዩ ላይ በሰፊው ከተወያየበት በኋላ ግብአቶችን በማከል ወደ ሕዝብ ተወካዮች ምክር ቤት እንዲተላለፍ በሙሉ ድምጽ ወስኗል፡፡

መስከረም 18 ቀን 2019 ዓ.ም

አዲስ አበባ

Previous articleታዳጊ ሀገራትን እንዴት ይታደጋል?
Next article🌊 የባሕር በር – ከቦሊቪያ ብሔራዊ ትርክት እስከ ኢትዮጵያ የሕልውና ጥያቄ።