
የሌማት ቱሩፋት መርሐ ግብር ሥርዓተ ምግብን ለማሻሻል፤ በምግብ ራስን ለመቻል እና የምግብ ሉዓላዊነትን ለማረጋገጥ የተጀመረ መርሐ ግብር ነው። አርብቶ አደሮችን እና አርሶ አደሮችን በማስተሳሰር የምግብ ዋስትናን ለማረጋገጥ የሚያስችልም ነው።
ለስኬታማነቱም ሁሉም ተባብሮ መርሐ ግብሩን በውጤታማነት እንዲፈጽም አቅጣጫ ተቀምጦ በክልሎች እና በከተማ አሥተዳደሮች ተግባራዊ ሲደረግ ቆይቷል።
በአማራ ክልል ደረጃም ለመርሐ ግብሩ ስኬታማነት በክልሉ ያሉ ጸጋዎችን መሠረት በማድረግ በግብዓት አቅርቦት፣ በቴክኖሎጂ ሽግግር፣ በሥልጠና እና በኤክስቴንሽን አገልግሎት ሰፊ ሥራዎች ተሠርተዋል። በዚህም ለክልሉ ኢኮኖሚ ተጨባጭ ውጤት አምጥቷል። ለአብነትም በዚህ በጀት ዓመት ለ157 ሺህ ወጣቶች በዘርፉ የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የተለያዩ አካባቢዎችን ተዘዋውረው በተመለከቱበት ወቅት እንደተናገሩት መርሐ ግብሩ ተግባራዊ ከተደረገ ጀምሮ ተስፋ ሰጭ ውጤቶች ተመዝግበዋል። በተለይም በዶሮ፣ በእንቁላል፣ በሥጋ፣ በወተት እና በማር ምርቶች ፈጣን እና መሠረታዊ ለውጥ እያመጣ መኾኑን ገልጸዋል።
ለአብነትም የማር ምርት ከሰባት እጥፍ በላይ ማደጉን ተናግረዋል። በዶሮ ሥጋ ምርት በአምስት ዓመታት ውስጥ ቀድሞ ከነበረው ከ48ሺህ ቶን ወደ 190 ሺህ ቶን ማደጉንም ገልጸዋል።
በዚህ ከቀጠለም ኢትዮጵያ በምግብ ራሷን በመቻል፣ ለውጭ ገበያ በማቅረብ፣ የውጭ ምንዛሬ በማግኘት፣ ብልጽግናን ለማረጋገጥ ለተጀመረው ጉዞ ትልቅ ማሳያ መኾኑን አመላክተዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
