የቀይ ባሕር ባይተዋርነት ያበቃል፤ የትውልድ የዘመናት ቁጭት በድል ይቋጫል።

6
ታሪክ ፍርደ ገምድል የሚኾንበት እና የፍትሐዊነት ሚዛንን የሚስትበት አጋጣሚ ብዙ ነው። በዓለም የታሪክ ማኅደር ውስጥ ታላቅ ሥልጣኔ ያላት ኢትዮጵያ ከራሷ ባሕር በር ተገፍታ በር አልባ እንድትኾን መገደዷ ለዚህ ትልቅ ማሳያ ይኾነናል።
ዘመናትን በተሻገሩ የውጭ ሴራዎች እና ሴራዎቹ የፈጠሯቸው የውስጥ መቆራቆዞች ተደማምረው የምሥራቅ አፍሪካዋን ግዙፍ ኃይል ሀገር በኢ-ፍትሐዊ መንገድ ከባሕር በሯ አግልለው በየብስ አጠሯት።
ሰፊ የመልማት አቅም እና አንጸባራቂ ታሪክ ይዞ የባሕር በር አልባ ከመኾን አልፎም ለወደብ ሌሎችን ደጅ መጥናት በርግጥም የኢትዮጵያውያንን ክቡር ማንነት የፈተነ ትልቅ የሕሊና ቁስል ነው።
ኢትዮጵያ እና ቀይ ባሕር የአንድ ሳንቲም ሁለት ገጽታዎች ናቸው። ይህም ሀገሪቱ በአንድ ወቅት ታሪኳ፣ ንግዷ እና ሥልጣኔዋ ከዚህ የባሕር በር ጋር በነበራት የማይናወጥ ቁርኝት ይገለጣል።
ኢትዮጵያ ያለባሕር በር የቱንም ያህል በተፈጥሮ ብትታደል፤ የቱንም ያህል በግዙፍ ፕሮጀክቶች ግንባታ እና ምርት ብትጥለቀለቅ፤ የቱንም ያህል የሕዝቦቿ ጥረት ቢታከልበት ዕድገቷን ምልዑ ሊያደርጉት አይቻላቸውም።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት “የባሕር በር ጥያቄ ካልተመለሰ ኢትዮጵያ ያሰበችውን ብልጽግና ማረጋገጥ እንደማትችል እና የ130 ሚሊዮን ሕዝብ ፍላጎት የጎረቤት ዕዳ ነው የሚኾነው” ማለታቸው ይታወሳል።
ላለፉት ሦስት አሥርት ዓመታት ኢትዮጵያውያን ይህንን የባሕር በር የይገባናል ጥያቄ ማንሳት እንደ ነውር ይቆጠርባቸው ነበር። አልፎ ተርፎም ተንኳሽ የሚል ስያሜም ያሰጣቸው ነበር። በዚህ የተነሳም ጉዳዩ በትውልድ ልብ ውስጥ ታፍኖ ለመቆየት ተገድዶ ነበር።
በመጨረሻም አጀንዳው ፍጹም አስገዳጅ ወቅታዊ እውነታ ላይ በመድረሱ ኢትዮጵያ ድምጿን ከፍ አድርጋ በዓለም አቀፍ መድረክ በይፋ ጥያቄዋን ማስተጋባት ከጀመረችም ዋል አደር ብሏል።
ለኢትዮጵያውያን የባሕር በር ባለቤትነትን ማስመለስ የታሪክን ፍርደ-ገምድልነትን ለማረም እና የትውልድ ሕልውናን ለማስቀጠል የሚደረግ ታሪካዊ ተጋድሎ ነው። ይህንን እውነት የተረዱ በርካታ የዓለም ሀገራት፣ ተቋማት እና ተጽዕኖ ፈጣሪ ግለሰቦችም ድጋፋቸውን እየገለጹ ይገኛሉ።
ይህም ኢትዮጵያ የባሕር በሯን ለማስመለስ የጀመረችው ተጋድሎ የመጀመሪያው ስኬት ነው። ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) ዓለም በጉዳዩ ላይ ስለሚያምንበት አግባብ ሲያብራሩም “ስለባሕር በር ጥያቄያችን ብዙዎችን አናግረናል፤ በአንድ አፍ ይገባችኋል፤ ነገር ግን በጦርነት መኾን ስለሌለበት ጊዜ ስጡን እንወያይበት ብለውናል” ነበር ያሉት።
ይህ አወንታዊ ምላሽ ኢትዮጵያ የጀመረችው የፍትሕ ጉዞ ትክክለኛ መሥመር ላይ መኾኑን ያንጸባርቃል። የባሕር በር ባለቤትነት ለኢትዮጵያውያን የመገፋት ታሪክ ማክተሚያ፤ የዕድገት በር መክፈቻ ቁልፍ እና በሌሎች ቸርነት ላይ ያልተንጠለጠለ የማይናወጥ ሀገራዊ ክብርን በመገንባት ወደ ቀደመው የታላቅነት ማማ መመለሻ ሕያው መወጣጫ መሰላል ነው።
በአድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየወጣቶችን ሕይወት በመቅረጽ ላይ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ልማት
Next articleየሌማት ቱሩፋት ስኬት፡ ከምግብ ዋስትና እስከ የውጭ ምንዛሬ ግኝት።