የወጣቶችን ሕይወት በመቅረጽ ላይ የሚገኘው የአረንጓዴ አሻራ ልማት

12
🐝ኢትዮጵያ ከጀመረቻቸው ኢኒሼቲቮች መካካል የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ቀደሚው ነው። ከ2011 ዓ.ም ጀምሮ ትኩረት ተሠጥቶት እየተሠራ ያለ ትልቅ ሀገራዊ እይታ ነው። ባለፉት ዓመታት በአረንጓዴ ልማት የተተከሉ ችግኞች አሁን ላይ ለበርካታ ወጣቶች እንጀራ መኾን ጀምረዋል።
ወጣቶች ሕይወታቸውን በንብ ማነብ ዘርፍ እንዲመሩም እያስቻላቸው ይገኛል። ሕይወታቸውን በዘርፉ ካስጠለሉት ወጣቶች መካከል የደብረ ማርቆስ ከተማ ነዋሪው ወጣት መለሰ ተፈራ እና ጓደኞቹ ይገኙበታል። እነዚህ ወጣቶች የተተከሉ ችግኞችን እየተንከባከቡ እና በንብ ማነብ ሥራ ተሠማርተው ለብዙ ወጣቶች አረዓያ መኾን ችለዋል።
ወጣቶች የቀፎዎችን ቁጥር እያሳደጉ መኾኑንም ይናገራሉ። በዚህም የተሻለ የማር ምርት በማግኘት በሥራቸው ውጤታማ መኾናቸውን ነግረውናል። ዘንድሮም ለንቦች ቀሰም የሚኾኑ የተለያዩ እፅዋቶችን መትከላቸውን አጫውተውናል። የወጣት መለሰ እና ጓደኞቹ ጉዞ ተፈጥሮን ጠብቆ እና አረንጓዴ አሻራን ከልማት ጋር አጣምሮ በመሥራት እራሱን ከድህነት ማላቀቅ እንደሚቻል ማሳያ ኾኗል።
በኢትዮጵያ ደን ልማት የአረንጓዴ አሻራ እና ሰው ሠራሽ ደን ልማት መሪ ሥራ አሥፈጻሚ አበሩ ጠና የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር ከተጀመረ ወዲህ በሀገሪቱ በርካታ ሁለገብ ለውጦች መመዝገባቸውን ገልጸዋል። መርሐ ግብሩ ከመጀመሩ በፊት በሀገር አቀፍ ደረጃ የተደረጉ ጥናቶች እንደሚያመለክቱት ከ54 ሚሊዮን ሄክታር በላይ መሬት ጉዳት ደርሶበት ነበር ይላሉ። ጉዳት ከደረሰበት ውስጥ 1 ሚሊዮን ሄክታር በላይ የሚኾነው መሬት በጣም የተጎዳ እንደነበር አንስተዋል።
በተከናወነው ተከታታይ የኾነ የአረንጓዴ አሻራ መርሐ ግብር የተጎዳው መሬት እንዲያገግም ተደርጓል ብለዋል። የሀገሪቱ የደን ሽፋን ከፍ እንዲል እና የተራቆቱ አካባቢዎች አረንጓዴ እንዲለብሱ ማስቻሉንም አስገንዝበዋል።
የችግኝ ተከላው ከደን ሽፋን ባለፈ የምግብ ዋስትናን ሊያረጋግጡ የሚችሉ የምግብ፣ የአትክልት እና ፍራፍሬ ልማት ላይ ልዩ ትኩረት ተሰጥቶ መሠራቱንም ጠቁመዋል። በተሠራው ሥራም የፍራፍሬ እና የአትክልት ምርትም እየጨመረ መምጣቱን ነው የተናገሩት።
በተለይም ችግኝ በማልማት፣ በአትክልት እና ፍራፍሬ፣ በንብ ማነብ እና በእንስሳት ማድለብ ሥራዎች በየዓመቱ ከ1 ሚሊዮን በላይ ወጣቶች እና ሴቶች ተጠቃሚ እየኾኑ እንደኾነ ነው የተናገሩት። ይህም የማኅበረሰቡን ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነት እያሳደገ ነው ይላሉ።
አረንጓዴ አሻራ አረንጓዴ የለበሰች ኢትዮጵያን ለትውልድ ለማሻገር የሚሠራ ታሪካዊ አሻራ መኾኑንም አመላክተዋል ።🌍
ዘጋቢ፦ ሥራውድንቅ ደሳለው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleአዲሱ መንግሥት መስከረም 25/2019 ዓ.ም ይመሰረታል።
Next articleየቀይ ባሕር ባይተዋርነት ያበቃል፤ የትውልድ የዘመናት ቁጭት በድል ይቋጫል።