“በጫካ የቆየሁበት ጊዜ ይጸጽተኛል”

41
ቀደም ሲል በትጥቅ ትግል በጫካ ሲንቀሳቀሱ ከነበሩት ታጣቂዎች መካከል ነው። በታጣቂዎቹ አጠራርም የክፍለ ጦር አሥተዳደር እና ስትራቴጂክ ጉዳዮች ኀላፊ በመኾን ሲንቀሳቀስ ቆይቷል።
አሁን ደግሞ ይሄዱበት የነበረው መንገድ የተሳሳተ መኾኑን በመረዳት የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በመቀበል በሰሜን ጎጃም ዞን በአንድ ወረዳ የሰላም እና ጸጥታ ጽሕፈት ቤት ውስጥ ሕዝብን እያገለገለ ይገኛል።
ባለ ታሪካችን እንደተናገረው የማኅበረሰቡን ጥያቄዎች በትጥቅ ትግል ብቻ ለማስመለስ የተደረገው ጥረት የተሳሳተ መንገድ እንደነበር በጸጸት ያስታውሳል። በጫካ ቆይታቸው ወቅት በማኅበረሰቡ ላይ ይደርስ የነበረው ግፍ፣ በደል እና ጭካኔ ሕሊናን የሚወቅስ እና ከባድ ስህተት እንደነበር ተናግሯል።
የሕዝብን ጥያቄ ለማስመለስ ማኅበረሰቡን ማሰቃየት ፍጹም ስህተት መኾኑን በመገንዘብ ሕዝብን እና ሀገርን ለመካስ ሰላምን ማስቀደም ብቸኛ አማራጭ መኾኑን አምነው ወደ መደበኛ ሕይወት መመለሳቸውን ገልጿል።
በአሁኑ ወቅት በተወከለበት ኀላፊነት ሕዝብን ከማገልገል ባሻገር የተረጋጋ እና ሰላማዊ ሕይወት እየመራ እንደሚገኝ የተናገረው ባለ ታሪካችን የታጠቁ አካላት ከሀገር ጠላቶች ጋር በመተባበር ሀገርን አሳልፎ መስጠት ተገቢ እንዳልኾነ እና ለሕዝብ ሰላም ቅድሚያ መስጠት እንደሚገባቸው አሳስቧል።
የሰሜን ጎጃም ዞን ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ገብረሥላሴ ታዘብ የዞኑ ሰላም ከጊዜ ወደ ጊዜ እየተሻሻለ መምጣቱን ገልጸዋል።
ከዚህ ቀደም የነበሩ የዘረፋ ድርጊቶች እና ሕገ-ወጥ እንቅስቃሴዎች በከፍተኛ ሁኔታ መቀነሳቸውን ጠቁመዋል። ይህም በተደረጉ ሰፊ ሕዝባዊ ውይይቶች እና ከጸጥታ መዋቅሩ ጋር በተደረገ ቅንጅታዊ ሥራ የተገኘ ውጤት መኾኑን አስረድተዋል።
በተሠራው ሥራም ትግሉ ትክክል አለመኾኑን በመገንዘብ እና በወቅታዊ ስሜት ተደናግረው ከነበሩበት ሁኔታ በመውጣት፣ በርካታ የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን ተቀብለው ወደ ማኅበረሰቡ መቀላቀላቸውን ተናግረዋል።
በአሁኑ ወቅትም በግል እና በቡድን የሰላም አማራጭን የሚቀበሉ አካላት ቁጥር እየጨመረ እንደሚገኝ ገልጸዋል። የሰላም አማራጭን ለሚቀበሉ አካላትም ወደ መንግሥት ሥራቸው እንዲመለሱ፣ በሰላም ማስከበር እና በተለያዩ የልማት ዘርፎች እንዲሰማሩ በማድረግ ኢኮኖሚያዊ ተጠቃሚነታቸው እየተረጋገጠ ይገኛል።
ቀደም ሲል የሥጋት ቀጣና የነበሩ አካባቢዎች ሰላማቸው በመሻሻሉ ነፃ የእንቅስቃሴ ሁኔታዎች መፈጠራቸውን የገለጹት ኀላፊው ትምህርት ቤቶች ሥራ እንዲጀምሩ ከማድረግ ባለፈ የተለያዩ መሠረተ ልማቶችን በመገንባት ማኅበረሰቡን ተጠቃሚ ማድረግ መቻሉን እና የመንግሥት አገልግሎትም በስፋት እየተሰጠ እንደሚገኝ አስታውቀዋል።
አሁንም የሰላም በሩ ክፍት በመኾኑ በጫካ ታጥቀው የሚንቀሳቀሱ አካላት ከታሪካዊ የሕዝብ እና የሀገር ጠላቶች ጋር ከመተባበር ወጥተው የሰላም መንገድን እንዲከተሉም ጥሪ አቅርበዋል።
ማኅበረሰቡም ለሰላም በመቆም ታጣቂዎች የሰላም አማራጭ እንዲከተሉ ተጽዕኖ በማድረግ የበኩሉን ድርሻ እንዲወጣም አስገንዝበዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleየሌማት ቱሩፋት ስኬት፡ ከምግብ ዋስትና እስከ የውጭ ምንዛሬ ግኝት።
Next article“የጥፋት እንቅስቃሴን በግንባር ቀደምትነት ለመፋለም እና ለመደምሰስ ዝግጁ ነን” የቀድሞ ታጣቂዎች