“የጥፋት እንቅስቃሴን በግንባር ቀደምትነት ለመፋለም እና ለመደምሰስ ዝግጁ ነን” የቀድሞ ታጣቂዎች

8
በደቡብ ጎንደር ዞን ከ800 በላይ የሚኾኑ የቀድሞ ታጣቂዎች የትጥቅ ትግል አማራጭን በመተው በሰላም ስምምነቱ ወደ ኅብረተሰቡ ተቀላቅለዋል።
ታጣቂዎቹ ወደ ሰላማዊ ሕይወት መመለሳቸውን ተከተሎ “ሀገር እንገነባለን እንጂ ሀገር አናፈርስም” በሚል መሪ መልዕክት ከዞኑ አሥተዳደር እና ከመከላከያ ሠራዊት ከፍተኛ የሥራ ኀላፊዎች ጋር የምክክር መድረክ ተካሂዷል።
በውይይቱ መልዕክት ያስተላለፉት የደቡብ ጎንደር ዞን ዋና አሥተዳዳሪ ጥላሁን ደጀኔ የባዕዳንን እና የውስጥ አጥፊዎችን የጥፋት ተልዕኮ በመሻር ወደ ሰላም መንገድ ለተመለሱት ወገኖች አድናቆት እና ምሥጋና አቅርበዋል።
“የሕዝብን ስም ሽፋን በማድረግ እና ከውስጥ እና ከውጭ ጠላቶች ጋር በመተባበር የሚሸረበውን ሴራ በመበጣጠስ በሰላም ስምምነቱ ወደ ሕዝብ መመለስ የእውነተኛ አሸናፊነት ማሳያ ነው” ብለዋል።
በሀገር መከላከያ ሠራዊት የምሥራቅ እዝ ተወርዋሪ ኮር ዋና አዛዥ ኮሎኔል ሰጥዬ አራጌ በበኩላቸው ኢትዮጵያውያንን ሀገር አልባ ለማድረግ ከውስጥ እና ከውጭ ተባብሮ የሚደረግን ሴራ አውግዘዋል።
የውጭ ወራሪን አሳፍሮ የመለሰን ታሪካዊ ሀገር ለመበተን የሚደረግ እንቅስቃሴ ከባድ የታሪክ ክህደት ነው” ያሉት ዋና አዛዡ በሰላም ስምምነቱ የተመለሱ ኀይሎች ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመሰለፍ የጸረ ሰላም ኀይሎችን የክፋት አጀንዳ በቁርጠኝነት ማክሸፍ እንዳለባቸውም አስገንዝበዋል።
የደቡብ ጎንደር ዞን ብልጽግና ፓርቲ ቅርንጫፍ ጽሕፈት ቤት ኃላፊ መንብር ክፈተው ባቀረቡት የውይይት የመነሻ ሰነድ እንደገለጹት የቀድሞ ታጣቂዎች የሰላም መንገድን መምረጣቸው እና ከመንግሥት ጎን መሰለፋቸው ለጠላቶች አንገት ያስደፋ ትልቅ ምዕራፍ ነው።
በተባበረ ክንድ የጥፋት ኀይሎችን እና የታላላኪዎችን አጀንዳ ለማምከን በትጋት እንደሚሠራም አስታውቀዋል።
በውይይቱ ላይ ከተሳተፉት የቀድሞ ታጣቂዎች መካከል መልካሙ ካሴ እና አዲሱ ደባልቄ ሕዝብን ለከፍተኛ መከራ እና ስቃይ የዳረገውን የተሳሳተ መንገድ በመገንዘብ ወደ ሰላም መምጣታቸውን ተናግረዋል።
አሁን ላይ ጥምረት ፈጥረናል በማለት የሚንቀሳቀሱ እና የሕዝብን ሰላም የሚረብሹ አካላትን የጥፋት እንቅስቃሴ በግንባር ቀደምትነት ለመፋለም እና ለመደምሰስ ዝግጁ መኾናቸውን አረጋግጠዋል።
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous article“በጫካ የቆየሁበት ጊዜ ይጸጽተኛል”