
በአማራ ክልል ላለፉት ሦሥት ዓመታት የተከሰተው የሰላም እጦት በማኅበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊ፣ ሥነ-ልቦናዊ እና መሠረተ-ልማት መስኮች ላይ በርካታ ቀውሶችን አስከትሏል። የዜጎችን ዕለታዊ የሕይወት እንቅስቃሴ ከመግታቱም በላይ የክልሉን አጠቃላይ የልማት እና የዕድገት ጉዞም ፈትኗል።
የሰላም እጦቱ ሰለባ ከኾኑት የክልሉ አካባቢዎች ደቡብ ጎንደር ዞን አንዱ ነው። ላለፉት ሦስት ዓመታት በዞኑ የተሟላ ሰላም ባለመኖሩ ለዘርፈ ብዙ ችግሮች ተጋልጠው መቆየታቸውን ነዋሪዎቹ አንስተዋል። ይሁን እንጅ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መኖሩን ገልጸዋል።
“የሰላም ማጣት ቀጥታ የሚጎዳው ሕዝቡን ነው” ያሉት ነዋሪዎቹ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት በርካታ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲመጡ ማድረጋቸውንም አንስተዋል።
ወንድም ወንድሙን ሲመክር የታጠቀው ኀይል ወደ ሰላም ይመለሳልም ብለዋል። በቀጣይም ቢኾን በዞኑ ዘላቂ ሰላም እና ደኅንነት እንዲሰፍን የበኩላቸውን ድርሻ እንደሚወጡም አረጋግጠዋል።
በደቡብ ጎንደር ዞን ባለፈው በጀት ዓመት የዞኑን ሰላም ለማስፈን ሕግ የማስከበር እና ሕዝባዊ ውይይቶች ሲከናወኑ መቆየታቸውን የዞኑ ሰላም እና ጸጥታ መምሪያ ኀላፊ ጌትነት በዛብህ ለአሚኮ ገልጸዋል።
በ2018 የበጀት ዓመት በዞኑ በተሠሩ የሰላም ማስፈን ሥራዎች በርካታ የታጠቁ ኀይሎች ወደ ሰላም እንዲገቡ መደረጉን ጠቅሰው በዚህም በዞኑ አሁን ላይ አንጻራዊ ሰላም መስፈኑን አስረድተዋል።
የመንግሥትን የሰላም ጥሪ በማይቀበሉ እና የዞኑን ሰላም ለማወክ በሚፈልጉ ኀይሎች ላይ ደግሞ ከሀገር መከላከያ ሠራዊት ጋር በመቀናጀት ሕጋዊ እርምጃ እየተወሰደ መኾኑን ኀላፊው ገልጸዋል።
አሁን ላይ ያለው የሰላም ሁኔታ ከባለፈው ዓመት ጋር ሲነጻጸር አንጻራዊ ሰላም የመጣበት መኾኑንም አብራርተዋል።
“ክልሉን ለታሪካዊ ጠላት አሳልፈን አንሰጥም” በማለት በርካታ የታጠቁ ኀይሎች የመንግሥትን የሰላም አማራጭ ተቀብለው እየገቡም ነው።
ሰላምን በማይቀበሉ አካላት ላይ ደግሞ ጠንካራ የሕግ ማስከበር ሥራ እንደሚሠራ እና ሕዝቡ ያጣውን ሰላም እና ደኅንነት አግኝቶ መደበኛ ሕይወቱን እንዲመራ በትኩረት እንደሚሠራም ኀላፊው አረጋግጠዋል።
የዞኑ ሕዝብ መረጃ በመስጠት፣ የታጠቁ ኀይሎችን መክረው እና ገስጸው ወደ ሰላም እንዲመጡ በማድረግ፣ እንዲሁም የጸጥታ መዋቅሩን በመደገፍ እና በማበረታታት ከፍተኛ አስተዋጽኦ እያበረከተ መኾኑንም ገልጸዋል።
በዞኑ ዘላቂ ሰላምን ለማስፈን በሚደረገው ጥረት መላው ሕዝብ እያደረገ ያለውን ትብብር አጠናክሮ ሊቀጥል እንደሚገባም ተመላክቷል።
ዘጋቢ፦ ቴዎድሮስ ደሴ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
