
ኢትዮጵያ የቀጣናዊ፣ አሕጉራዊ እና ዓለም አቀፋዊ ድርጅቶች መቀመጫ በመኾን በርካታ ዓለም አቀፍ እና አሕጉራዊ ኮንፈረንሶችን በማስተናገድ የምትታወቅ ሀገር ናት።
ለአፍሪካ ኅብረት በቋሚነት መቀመጫ በመኾን፣ የኅብረቱን ጉባኤዎች ታስተናግዳለች። ሌሎች የዓለም አቀፋዊ መድረኾችንም በስፋት በማስተናገድ የቀደመ የዲፕሎማሲ ማዕከልነቷን እና መዳረሻነቷን ዛሬም አስቀጥላለች።
የአማራ ክልልም ልዩ ልዩ ታላላቅ መድረኮችን በማስተናገድ በኮንፈረንስ ቱሪዝም ሰፊ አቅም እንዳለው የአማራ ክልል ባሕል፣ ቱሪዝም እና ስፖርት ቢሮ የቱሪዝም አገልግሎት ዳይሬክተር ደጀኔ አከለ ያብራራሉ።
በክልሉ በዓለም አቀፍ የጥራት ደረጃ የተመዘኑ በርካታ ሆቴሎች መኖራቸውንም አንስተዋል። እነዚህ ሆቴሎች ሀገር አቀፍ፣ አሕጉራዊ እና ዓለማቀፋዊ ኮንፈረንሶችን በብቃት የማስተናገድ አቅም እንዳላቸው ተናግረዋል።
በዚህም አሁን ላይ ክልሉ ማንኛውንም ኮንፈረንሶች የማስተናገድ አቅም እንዳለው አብራርተዋል። ለአብነትም ባሕር ዳር ከተማ የጣና ፎረምን የዘንድሮን ጨምሮ ለ12 ዓመታት ማስተናገዷ የዚሁ ማሳያ መኾኑን አንስተዋል።
በክልሉ እንግዳን ተቀብሎ በእንክብካቤ በማስተናገድ ጥሩ ልምድ አለ ነው ያሉት። ሆቴሎች እና የአገልግሎት ሰጭ ተቋማትም ለሀገር ውስጥ እና ለውጭ እንግዶች የሚያስፈልገውን አገልግሎት በአይነት እና በጥራት አሟልተው ሁሌም ዝግጁ መኾናቸውን ተናግረዋል።
እንግዶች በሥብሠባ ከመሳተፍ በተጨማሪ በተለያዩ ቦታዎች እየተንቀሳቀሱ የሕዝቡን ባሕል፣ ታሪኩን፣ የተፈጥሮ ጸጋዎችን እና ሌሎችን የመስህብ ሀብቶች መጎብኘት እንደሚፈልጉም ጠቁመዋል።
ማኅበረሰቡም እንግዶች በሚሄዱበት ቦታ ሁሉ በአግባቡ ተቀብሎ በማስተናገድ ጸጋዎችን በማስተዋወቅ የክልሉን ገጽታ የመገንባት ኅላፊነቱን መወጣት እንደሚገባው ጠቁመዋል።
የባሕር ዳር ከተማም ባለፉት ዓመታት ያካበተችውን ኮንፈረንሶችን የማስተናገድ ልምድ በመጠቀም 12ኛውን የጣና ፎረምም በብቃት እያስተናገደች ትገኛለች።
#የመደመር_መንግሥት!#ትልቅ_ሀገር_ትልቅ_ሕዝብ_ታላቅ_ርዕይ!🇪🇹
#ባሕር_ዳር #ጥቅምት_13_2019_ዓ_ም
✍️ዘጋቢ:- አሰፋ ልጥገበው
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
