በተራራዎች የተከበበችው የሰላም ወደብ፤ የሰው ማዕበል የሚፈስስባት አምባሰል

9
የመስቀሉ ደመራ ጨለማውን በብርሃን ይተካል። ከዚያም የምዕመናን ልብ ወደ ግሸን ደብረ ከርቤ ይሸፍታል። ግሸን በአማራ ክልል በደቡብ ወሎ ዞን አምባሰል ወረዳ ውስጥ ትገኛለች።
ከደሴ ከተማ ያላት ርቀትም በስተሰሜን አቅጣጫ 76 ኪሎ ሜትር ላይ ነው። አምባዋ አንድ መግቢያ በር ብቻ አላት። ዙሪያዋም በገደል የተከበበ ነው። የላይኛው ክፍሏ ሜዳማ እና የመስቀል ቅርጽ አለው።
ቅድስቷ ተራራ በርካታ ስያሜዎች ነበሯት። በ11ኛው ክፍለ ዘመን አጼ ላሊበላ “እግዚአብሔር አብ” የተሰኘ ቤተ ክርስቲያን አነጹባት። በዚህም “ደብረ እግዚአብሔር” ተባለች ይባላል። ቀጥሎም “ደብረ ነገሥት” የሚል ስም አገኘች።
በሐይቅ እስጢፋኖስ ገዳም ሥር ስትተዳደር ደግሞ “ደብረ ነጎድጓድ” ተብላለች። ስሟ ወደ “ደብረ ከርቤ” የተቀየረው በ14ኛው መቶ ክፍለ ዘመን ነው። ይኸውም በአጼ ዘርዓ ያዕቆብ ዘመነ መንግሥት የክርስቶስ ግማደ መስቀል ወደ ሥፍራዋ ሲገባ ነው።
ግማደ መስቀሉ ከእስክንድርያ ስናር የመጣው መስከረም 10 ቀን ነው። ከዚያም ወደ ግሸን አምባ መጣ። አጼ ዘርዓ ያዕቆብም መቅደስ ሠርተው አኖሩት። ይህንንም ለመላው ኢትዮጵያ በመስከረም 21 ቀን በአዋጅ አስነገሩ። ይህ ታሪካዊ ዕለትም በየዓመቱ በድምቀት ይከበራል።
የግሸን አምባ ዓመታዊ የንግሥ በዓል ጥልቅ መንፈሳዊ ትርጉም አለው። የሰው ልጅ ከፈጣሪው ጋር የሚያደርገውን የፍቅር እና የናፍቆት ግንኙነት ያሳያል።
ምዕምናን ነጭ ነጠላ ለብሰው ወደ ሥፍራው ያቀናሉ። እሾህ እና አሜኬላው፣ ቁልቁለቱ እና አቀበቱ አያግዳቸውም። ምድሪቱ በሰው ማዕበል ትጥለቀለቃለች። በጉዞው ላይ የሰውነት ድካም በመንፈስ ሐሴት ይዋጣል።
በዕለቱ ካህናቱ ውብ አልባሳትን ይለብሳሉ። ጽናጽል እና ከበሮ ይመታሉ። መቋሚያውን እያወዛወዙ ያሬዳዊ ዜማን ያሰማሉ። ጣዕመ ዜማው በግሸን ሸለቆዎች ውስጥ የገደል ማሚቶውን ያስተጋባል። ዝማሬው እና የእጣኑ ጢስ ምድራዊውን ከሰማያዊው ዓለም ያስተሳስራል።
የግሸን ደብረ ከርቤ በዓል የታሪክ እና የእምነት ሕያው ሙዚየም ነው። ነጭ የለበሰው ሕዝብ በእምነት አንድ ይኾናል። በዘር፣ በቋንቋ እና በማኅበራዊ እርከን ሳይከፋፈል ፈጣሪውን በአንድነት ይጠራል።
ግሸን ማርያም ዘመናትን የተሻገረች የኢትዮጵያውያን የነፍስ መጠጊያ እና የሰላም ወደብ መኾኗን ዘንድሮም ልታስመሰክር እንግዶቿን እየተጠባበቀች ነው።
#ባሕር_ዳር: መስከረም 13/2019 ዓ.ም
በስማቸው አጥናፍ
‎የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
Previous articleወንድም ወንድሙን ሲመክር ሰላም ይመለሳል።
Next articleበወገራ ወረዳ በጫካ ሲንቀሳቀሱ የነበሩ ታጣቂዎች የሰላም አማራጭን መቀበላቸውን ቀጥለዋል።