
ቀደም ባሉት ዓመታት የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ መዋቅራዊ ችግሮች እንደነበሩበት መረጃዎች ያሳያሉ። ሀገሪቱም ከፍተኛ የማክሮ ኢኮኖሚ አለመረጋጋት ውስጥ ገብታ እንደነበር የዘርፉ ባለሙያዎች ያረጋግጣሉ።
በዚህ የተነሳም ኢትዮጵያ ጥቁር ገበያ የተስፋፋባት፤ የኤክስፖርት አፈጻጸሟ ዝቅተኛ የኾነች፤ የፋይናንስ እጥረት ያለባት፤ የውጭ ዕዳ መክፈል የማትችል፤ የመሠረታዊ ሸቀጦች ዋጋ እና የነዋሪዎች የመግዛት አቅም ፍጹም የተራራቀባት ሀገር ኾና እንደነበር ይነሳል።
በዚያ ወቅት በኢኮኖሚው ላይ መንግሥት ከፍተኛ ተዋናኝ ነበር። በአንጻሩ የግሉ ዘርፍ ለሀገሪቱ የኢኮኖሚ ዕድገት አስተዋጽኦ የሚያደርግበት ሁኔታ አልነበረም።
ይህንን ችግር በመቅረፍ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ መዋቅር ለማዘመን እና የማክሮ ኢኮኖሚ መረጋጋትን ለማምጣት “ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ” ተግባራዊ መደረጉ ይታወሳል። ማሻሻያው በከፍተኛ ቁርጠኝነት ተተግብሮ ለኢትዮጵያ ተጨባጭ ውጤቶችን እንዳስገኘ ይነገራል።
የኢትዮጵያ ሀገር በቀል የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያ የሀገር ውስጥ መረጋጋትን እና ተዓማኒነትን መልሶ ማምጣቱን የኢትዮጵያ ብሔራዊ ባንክ ገዥ እዮብ ተካልኝ (ዶ.ር) በአንድ ወቅት መናገራቸውን ይታወሳል።
ማሻሻያውን ውጤታማ ለማድረግ ማሻሻያው ከመደረጉ በፊት ከነበረው በተሻለ መንገድ የዋጋ ንረትን የመቆጣጠር፤ የውጭ ምንዛሬ ገበያውን ነጻ የማድረግ፤ የገንዘብ እና የፊስካል ፖሊሲን የማዘመን፣ ለዘላቂ እና አካታች ዕድገት ጠንካራ መሠረት ለመጣል የፋይናንስ ዘርፉን የማጠናከር ሥራ ተከናውኗል ነው ያሉት።
ጠቅላይ ሚኒስትር ዐቢይ አሕመድ (ዶ.ር) የማክሮ ኢኮኖሚ ሪፎርሙ ለኢትዮጵያ ኢንዱስትሪ ውጤታማነት እና ለኢትዮጵያ ምርታማነት ከፍተኛ ለውጥ ማምጣቱን ገልጸዋል። ሪፎርሙ በጣም የዘገየ ነገር ግን ሥር ነቀል የሚባል ሥራ መኾኑን ጠቅሰዋል። የተገኘው ውጤትም በቀላሉ የሚታይ አለመኾኑን መግለጻቸው ይታወሳል።
👉 የማክሮ ኢኮኖሚ ማሻሻያው ዓላማ፦
✅ ገበያውን ክፍት በማድረግ ሰዎች የሚተማመኑበት የንግድ ከባቢን መፍጠር፤
✅ የመንግሥት የልማት ድርጅቶች በገበያው ውስጥ እንደማንኛውም ድርጅት የሚወዳደሩበት በማድረግ የግሉን ዘርፍ ይዞታ ማስፋት መኾኑንም ጠቅሰዋል።
ከዚህ አኳያ ማሻሻያው ከተደረገ በኋላ እያንዳንዱ ኩባንያ በፖለቲካል ኮሚቴ እንደማይመራ ጠቁመዋል። ትርፋማ መኾንን ታሳቢ ባደረገ የቢዝነስ ሕግ እንደሚሠራም ነው ያስገነዘቡት።
ሌላው ማሻሻያ የተደረገበት የፋይናንስ ዘርፍም ብሔራዊ ባንክ ፣ ፋይናንሻል ትራንዛክሽን፣ ካፒታል ገበያ፣ የመንግሥት ወጭ እና ገቢ አሥተዳደር ላይም ለውጥ ማምጣቱን ተናግረዋል።
ሪፎርሙ በውጤት ደረጃ ሲታይ የውጭ ምንዛሬ አቅርቦት፣ ኤክስፖርት በመጨመር እና ተኪ ምርትን በማሳደግ ውጤት ማስገኘቱን ገልጸዋል።
#አሚኮ #ECONOMICREFORM #ETHIOPIA 🇪🇹
#ባሕር_ዳር #መስከረም_12_2019_ዓ_ም
ዘጋቢ፦አድኖ ማርቆስ
የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!
