የመስቀል በዓልን በስኬት ለማክበር በቂ ዝግጅት ተደርጓል።

14

 

የመስቀል ደመራ በዓል በሁሉም የክልሉ አካባቢዎች ያለምንም የጸጥታ እንከን በድምቀት እንዲከበር የተጠናከረ ዝግጅት ማድረጉን የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ አስታውቋል።

የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ የመስቀል በዓልን ምክንያት በማድረግ መግለጫ ሰጥቷል።

መግለጫውን የሰጡት የአማራ ክልል ፖሊስ ዋና ጠቅላይ መምሪያ ምክትል ኮሚሽነር ጄኔራል እና የወንጀል መከላከል ጠቅላይ መምሪያ አዛዥ ምክትል ኮሚሽነር አበበ ውቤ በዓሉ የሰላም እና የፍቅር መገለጫ ነው ብለዋል።

በስኬት እንዲከበርም የፌዴራል እና የክልሉን የጸጥታ መዋቅሮችን ያካተተ ዝርዝር ዕቅድ ታቅዶ ወደ ሥራ መገባቱንም ጠቁመዋል።

የጸጥታ ኀይሉ ብቻ ሳይኾን መላው ሕዝብ፣ ወጣቶች እና የሃይማኖት አባቶች በባለቤትነት ተሳታፊ እንዲኾኑም እየተሠራ ነው። በተለይም ደመራው በሚነድባቸው አካባቢዎች ቅድመ ፍተሻዎችን የማድረግ እና ቦታዎችን የማስተካከል ሥራ ቀድሞ መሥራት እንደሚገባም ነው ያስታወቁት።

ሕዝቡ የራሱን ደኅንነት በራሱ እንዲጠብቅ የሚያስችል የብሎክ አደረጃጀት መዘርጋቱንም ጠቁመዋል።

በበዓሉ ወቅት ሊያጋጥሙ የሚችሉ የጸጥታ ሥጋቶችን ከመቀነስ አኳያም ሕፃናት እና ወጣቶች አላስፈላጊ ከኾኑ ተተኳሾች እና ርችቶች እንዲቆጠቡ አስቀድሞ እየተሠራ ነው ብለዋል። ሕዝቡ አጠራጣሪ ነገሮችን ሲመለከት በፍጥነት እንዲጠቁምም ጥሪ አቅርበዋል።

የትራፊክ አደጋን ለመከላከል እና ትርፍ ጭነትን ለመቆጣጠር ከመናኸሪያ ጀምሮ ለሾፌሮች፣ ለደንብ አስከባሪዎች እና ለተሳፋሪዎች በቂ ግንዛቤ ተሰጥቷል ነው ያሉት። የትራፊክ ፍሰቱ በተገቢው መንገድ እንዲመራ እና መንገዶች ደኅንነታቸው የተጠበቀ እንዲኾን የጸጥታ አካላት በጥምረት እየሠሩ ነው ብለዋል።

በመስቀል ደመራ የጎብኝዎች ቁጥር የሚጨምርበት ነው። በበዓሉ ወቅት ወደ ባሕር ዳር፣ ጎንደር፣ ላሊበላ፣ ጢስ ዓባይ እና የተለያዩ ገዳማት የሚመጡ የሀገር ውስጥ እና የውጭ ቱሪስቶች ያለምንም ሥጋት በሰላም እንዲንቀሳቀሱ እና በዓሉን እንዲያከብሩም ልዩ ትኩረት መሰጠቱን ተናግረዋል።

ከመደበኛው የጸጥታ አጠባበቅ ባሻገር ድንገተኛ ክስተቶች ቢያጋጥሙ ፈጣን ምላሽ የሚሰጥ ልዩ የምርመራ ቡድን መዘጋጀቱንም ተናግረዋል።

#አሚኮ #የመስቀልደመራ #ፖሊስ #አማራክልል #ኢትዮጵያ🇪🇹

#ባሕር_ዳር #መሥከረም _12_2019_ዓ_ም

ዘጋቢ፦ ስማቸው አጥናፍ

የአሚኮ ዲጂታል ሚዲያ ቤተሰብ ይሁኑ!

Previous article“ከጥቁር ገበያ መስፋፋት ወደ መዋቅራዊ ለውጥ፤ የሀገር በቀል ኢኮኖሚው ማሻሻያ ፍሬ”
Next article“የኢትዮጵያ የባሕር ኀይል ዳግም ትንሣኤ”